ዕሁድ የተካሄደው የበኒን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቅድመ ውጤት ዛሬ ይገለጻል ተብሎ እየተጠበቀ ነው። ምርጫው ተጭበርብሯል ብለው ተቃዋሚዎች እየከሰሱ ቢሆንም ፕሬዚዳንቱ ፓትሪስ ታሎን አሸንፈው ለሁለተኛ የአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመን መንበሩ ላይ ይቆያሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው።
ፕሬዚዳንቱን ተፎካካሪዎቻቸውን ከውድድሩ ውጪ የሚያደርግ የምርጫ ህግ አውጥተዋል ወይም የግዳቸውን ሃገር ጥለው እንዲሰደዱ አድረገዋል ብለው የከሰሱዋቸው ተቃዋሚ መሪዎች ህዝቡ በምርጫው እንዳትሳተፉ የሚል ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
የፕሬዚዳንቱ ደጋፊዎች በበኩላቸው የምርጫ አስፈጻሚ ባለሥልጣኑ የእሁዱ ምርጫ በአብዛኛው በሰላም ተከናውኗል ማለታቸውን እየጠቀሱ የተጭበረበረ ነገር የለም በማለት እየተከራከሩ ናቸው። ከምርጫው በፊት የሰው ህይወት የጠፋባቸው ግጭቶች የነበሩ ቢሆንም የምርጫው ያለምንም የጎላ ችግር እንደተፈጸመ ነው የምርጫ ባለሥልጣኑ የተናገሩት።
ይሁን እንጂ ምርጫ ያልተካሄደባቸው አካባቢዎች ነበሩ፤ የምርጫ አስፈጻሚው ኮሚሽን ባለሥልጣን ከ546 ወረዳዎች በአስራ ስድስቱ ምርጫው ሊካሄድ እንዳልቻለ ገልጸዋል፤ ለምን እንደሆነ አላብራሩም።
በሌላ በኩል አንድ የሀገሪቱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ማህበር መራጮች ላይ የማስፈራራት እና የማዋከብ አድራጎት መፈጸሙን በመቶዎች የተቆጠሩ የምርጫ ታዛቢዎች ሪፖርት ማቅረባቸውን አስታውቋል።