ዋሺንግተን ዲሲ —
ዝነኛው ድምፃዊ አቤል ተስፋዬ /ዘ ዊክንድ/ በኢትዮጵያ በረሃብ ላይ ለሚገኙ ዜጎች የሚውል የአንድ ሚሊዮን ዶላር እርዳታ መለገሱን ገለፀ።
ከኢትዮጵያውያን ወላጆች በካናዳ ተወልዶ ያደገው፣ ዕውቁ ድምፃዊ፣ የግጥም፣ የዜማ ደራሲ እና ሙዚቃ ፕሮዲዮሰር ዘ ዊኬንድ፣ እርዳታውን አስመልክቶ በትዊተር ገፁ ባሰፈረው ጽሁፍ
"በህዝቤ፣ በኢትዮጵያውያን ህጻናት እና አረጋዊያንን ጨምሮ ያለምክንያት የሚፈጸመው ግድያ፣ ነዋሪዎች በፍርሃት እና በመንደሮቻቸው ላይ በደረሰው ውድመት የተነሳ መፈናቀላቸው ልቤን ሰብሮታል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም አማካይነት ሁለት ሚሊዮን ዜጎችን ለመመገብ የሚውል አንድ ሚሊዮን ዶላር ለግሻለሁ፤ ሌሎቻችሁም የምትችሉትን እንድትለግሱ ጥሪዬን አቀርባለሁ" ብሏል።
ድምፃዊው አቤል ተስፋዬ የለስገሰውን እርዳታ አስመልክቶ ትናንት መግለጫ ያወጣው በዩናይትድ ስቴትስ ለዓለም የምግብ ፕሮግራም ድጋፍ ለማሰባሰብ የሚሰራው /WFP USA/ ይህ ትልቅ እርዳታ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል በግጭቱ ምክንያት ለተጎዱ ዜጎች ነፍስ አድን የምግብ እርዳታ ለማቅረብ እንደሚውል አስታውቋል።