በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ካፒቶል በደረሰ ጥቃት ፖሊሶች ተጎዱ


ዛሬ አርብ ዩናይትድ ስቴትስ መዲና ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ አንድ አሽከርካሪ መኪናውን የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ህንጻ ካፒቶል መከለያ አጥር ጋር አጋጭቶ ባደረሰው ጥቃት ጉዳት ከደረሰባቸው ሁለት የካፒቶል ፖሊስ አባላት አንደኛው ወደሆስፒታል ከተወሰደ በኋላ ህይወቱ ማለፉ ተገልጿል።

የዩናይትድ ስቴትስ ካፒቶል ፖሊስ እንዳስታወቀው መኪናውን ከካፒቶል መከለያ አጥሩ ጋር ያጋጨው ተጠርጣሪ መሳሪያ ይዞ ከመኪናው ውስጥ ወጥቶ እንደነበር ሆኖም ወዲያው በቁጥጥር ስር ውሏል።

ተጠርጣሪው በአስጊ ሁኒታ ላይ እንደነበር እና ጥቂት ቆይቶ ህይወቱ እንዳለፈ የህግ አስከባሪ ምንጮች መናገራቸውን አሶሼየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

ሁኔታው የተከሰተው በዩናይትድ ስቴትስ ካፒቶል ህንጻ በመወሰኛው ምክር ቤት ክንፍ በኩል ኮንስቲቲዩሽናል አቨኑ በሚባለው መንገድ በኩል ባለው የመግቢያ ፍተሻው ቦታ ላይ መሆኑ ታውቋል።

የፌዴራል ምርመራ ቢሮ የዋሽንግተን መስክ ቢሮ በክትትሉ እየረዳ መሆኑ ተገልጿል።

ባለፈው ጥር ወር የወቅቱ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ ደጋፊዎች የምክር ቤት አባላቱ ለተመራጭ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን የተሰጡትን ድምጾች ቆጥረው ለማረጋገጥ በተሰበሰቡበት ወቅት ቆጠራውን ለማስቆም ምክር ቤቱን ወርረው ጥቃት ካደረሱ ወዲህ የምክር ቤት ህንጻው ዙሪያውን ታጥሯል፤ የውጭው አጥር በዚህ ሳምንት የተነሳ ቢሆንም አሁንም የውስጠኛው አጥር ህንጻውን ዙሪያውን እንደከለለ ነው።

ባሁኑ ጊዜ ምክር ቤቱ ለዕረፍት ዝግ በመሆኑ አብዛኞቹ አባላት ወጥተዋል። የመወሰኛ ምክር ቤቱ የውህዳኑ ሪፐብሊካኖች መሪው ሴኔተር ሚች መኮነል በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ቃል "በጥቃቱ ለተጎዱት የካፒቶል ፖሊስ አባላት እንጸልያለን፣ የዩናይትድ ስቴትስ ካፒቶል ፖሊስንና በስፍራው ተገኝተው ድጋፍ እየሰጡ ያሉትን ፈጥኖ ደራሾች እናመሰግናለን" ብለዋል።

XS
SM
MD
LG