የዛሬ 46 ዓመት ገደማ አዲስ አበባ ውስጥ የተወለደው ማውንስ ክላውሰን ወደ ሲዊድን ሲመጣ ገና የ10 ወር ጨቅላ እንደነበረ ይናገራል። ከጉዲፈቻ ድርጅት የሰሙትን ያመኑት አሳዳጊዎቹ የተረዱት ወላጅ እናቱ በህይወት እንደሌሉ ነበር።
የዛሬ ሁለት ዓመት ከግማሽ ከአንድ አፈላላጊ ተቋም የደረሰው ማህደር ግን ከተነገረው የተለየ ዕውነታን አበሰረው። ፎቶና ደብዳቤዎችን ያካተተው ማህደር ወላጅ እናቱ በህይወት እንዳሉ፣ እሱን ማግኘት እንደሚፈልጉም ያሳያል።
ማውንስ ተቋሙ ባመቻቸው የመገናኛ መንገዶች በኩል ከእናቱ እና ከሌሎች የስጋ ዘመዶቹ ጋር የርቀት ግንኙነት ጀመረ።
ማውንስ ክላውሰን ሲውዲን ውስጥ አድጎ በተወናይነት ስራ ላይ የተሰማራ የኪነጥበብ ሰው ፣የአደባባይ ተናጋሪም ነው። የአደባባይ አንቂነቱ እና የኪነጥበብ ሰውነቱ ግን ከአራት አስርት ዓመታት በኃላ ወላጅ እናቱን በሚያገኝበት ጊዜ የተሰማውን ድበልቅልቅ ስሜት ለመግለጽ አቅም ያነሰው ይመስላል።
“ደብዳቤው ከደረሰኝ ከጥቂት ወራት በኃላ ወደ አዲስ አበባ በረርኩ። ሁኔታው የእውን የማይመስል ስሜት ነበረው።በጣም የሚያስገርምም ነበር።አግኝቻት የማላውቃት፣ ለእኔ እንደ እንግዳ የሆነችብኝ እናቴ በዚያ ነበረች።ለእሷ ግን ለ46 ዓመታት ያክል ስታፈላልገኝ የነበርኩት ልጇ ነኝ ። ያንን ስሜት ዕውን የማይመስል ፣ እንደ ህልም የሆነ የሚለውን ቃል አዘውትሬ በመጠቀም ልገልጸው እሞክራለሁ ’’፣ ብሎል ለአሜሪካ ድምጽ ።
ሀገር ቤት የሚገኙ ወንድሞቹ እና እናቱ ያቀረቡትን መረጃ በማደራጀት ፣ማውንስ ክላውሰን እና እናቱ ለመገናኘት እንዲችሉ ያገዘው ተቋም ቤተሰብ ፍለጋ ይባላል።
የድርጅቱ መስራች አሜሪካዊቷ አንድሪያ ኬሊ ይባላሉ ። በጉዲፈቻ የወሰዷቸውን ዛሬ ታዳጊ ወጣት የሆኑ ሁለት ልጆቻቸውን የስጋ ዘመዶች ለማግኘት ለበርካታ ዓመታት ለፍተዋል፣።በእነዚያ ዓመታት ካዩት እና ከተረዱት ተነስተው ተቋሙን ለመመስረት እንደተነሳሱ ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ካለተርፍ በተቋቋመ ድርጅት ደንብ የተመዘገበው “ቤተሰብ ፍለጋ” በመረጃ ቋቱ ውስጥ ከ1000 በላይ በጉዲፈቻ የተሰጡ ትውልደ ኢትዯጵያዊያንን የሚመለከቱ መረጃዎችን ይዟል። ከተመሰረተበት የአውሮፓዊያን 2015 ወዲህ ከ200 በላይ የተጠፋፉ ፣በጉዲፈቻ የተወሰዱ ልጆችን ሀገር ቤት ከሚገኙ የስጋ ዘመዶቻቸውን እንዳገናኘ የድርጅቱ መስራች ነግረውናል።
በጉዲፈቻ የተሰጠ ልጅ አሊያም ዘመድ ያላቸው ሰዎች ፣ ወይንም ደግሞ በጉዲፈቻ ተሰጥተው ያደጉ እና የስጋ ዘመዶቻቸውን ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ለአውታሩ ያሏቸውን መረጃዎች ይልካሉ።
በገጹ ላይ የሚወጣውን “የአፋልጉኝ መረጃን” በማየት የሚገናኙ ሰዎች የመኖራቸውን ያህል፣ የድርጅቱ ተቀጣሪ የማህበረሰብ ሰራተኞችን ተጨማሪ ስራ የሚጠይቁ ጉዳዮችም አሉ።ቢሮክራሲ እና ማህበረሰባዊ ትብብር ማነስ በፍለጋው የሚሰማሩትን ሰራተኞች ስራ አልፊ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል እንደሚጠቀሱ የድርጅቱ ባልደረባ ሀብታሙ ዓለማየሁ ይናገራሉ።
“ ስራው ፈታኝ ነው!” ይላሉ በድርጅቱ ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል ማገልገላቸውን የሚናገሩት አቶ ሀብታሙ ፣ “በመጀመሪያ እንደምታውቀው የዚህ ሀገር ቢሮክራሲ ፈታኝ ነው።ሁሉም አካላት ተባባሪ ሊሆኑ አይችሉም። ጥቂቶች አላማህን ሊረዱ ይችላሉ።ምናልባት ፖሊስ ላይ ሄደህ ስትጠይቅ ፣መረጃ ስጡኝ ስትል አንሰጥህም ሊሉ ይችላሉ።ህጋዊ ተወካይ ሆነህ እያለ (መረጃ) ልትከለከል ትችላለህ።የወረዳ ሰዎችም ላይተባበሩህ ይችላሉ።በዚህ አጋጣሚ ግን የተባበሩንም አሉ። እነሱን አመሰግነን ማለፍ አለብን ” ሲሉ ፈተናዎቹን ያስረዳሉ።
በዓመታት ውስጥ የስፍራዎች እና ሁኔታዎች መለዋወጥ፣ ማህበረሰቡ አፈላላጊዎች የሚፈልጉትን መረጃ ለመስጠት ተጠራጣሪ መሆኑ፣ አንዳንዴም ፈቃደኛ አለመሆኑ ስራውን ፈታኝ እንዳደረገው ይጠቁማሉ።
እነዚህ እና መሰል ተግዳሮቶች ተቋቁሞ ለሰባት ዓመታት ያህል የዘለቀው ተቋም ፣ ልፋቶቹ ለፍሬ በቅተው ለሰዎች ደስታ እና እፎይታን ሲያመጣ ማየት ያለውን ልዩ ስሜት አቶ ሀብታሙ ሲያስረዱ ፣
“ልጆቻቸውን በጉዲፈቻ ከሰጡ በኃላ ኢትዮጵያዊ(የሀበሻ) ቀሚስ መልበስ ያቆሙ፣ ኢትዮጵያዊ እናት አይደለሁም ፣ ልጄን እኮ ማሳደግ አልቻልኩም ብለው ያፈሩ ፣ የተጨነቁ እራሳቸውን እንደ ሰው የማይቆጥሩ ፣ ነገር ግን እኛ ስናገናኛቸው 'አሁን ገና እናት ሆነናል፣ አሁን ገና እንደገና መኖር ጀመርን ፣ ከሞት ነው ያነሳችሁን!' የሚሉን ብዙ ናቸው።ይህ ለኢትዮጵያዊያን ዳግም ህይወት መስጠት ነው ” ብለዋል።
አንድሪያ ኬሊ ከግል ፈተናቸው ተነስተው የጀመሩት አውታር በመላ ዓለም የተበተኑ እና የስጋ ዘመዶቻቸውን ለማወቅ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን ብሎም የልጆቻቸውን መገኛ ላላወቁ ወላጆች የቅርብ ተስፋ እየሆነ የመጣ ይመስላል። ስለ አውታሩ ሌሎች ሰዎችም ሰምተው በፍለጋው ትስስር ውስጥ እንዲሳተፉ ጥሪ ያቀረቡት መስራቿ ፣ ተቋሙ በቅርቡ የሚጀምራቸው አዳዲስ አሰራሮች በርከት ያሉ ሰዎችን ለዐይነ ስጋ ለማብቃት ያስችላሉ ብለው ተስፋ ሰንቀዋል።
“በቅርቡ የምንጀምራቸው አዳዲስ ስራዎች አሉ። የዘረ መል መረጃ ቋት ይኖረናል።አንድን ልጅ ብቻ ከመፈለግ ይልቅ በርከት ያሉ ሰዎችን በአንድ ፍለጋ ለማገናኘት ያግዘናል።ዘመዶቻቸውን የሚፈልጉት ልጆች አብዛኞቹ በአሳዳጊዎቻቸው አማካይነት የዘረ- መል ናሙና ይሰጣሉ።በርካታ ሰዎች ምርመራ እንዲያደርጉ ማድረግ ይቻላል። ይሄ በጣም ጥሩ መንገድ ነው” ፣ ብለዋል አንድሪያ ።
ድርጅቱ በኢትዮጵያዊያን ቤተሰቦች በኩል የሚቀርቡ የ"አፈላልጉልኝ" ጥያቄዎችን በነጻ እንደሚያስናግድ የሚናገሩት አንድሪያ በቅርቡ ደግሞ በጉዲፈቻ ተወስደው በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ለስራ ያልደረሱ ወጣቶችን ፣ አሊያም ከአሳዳጊዎቻቸው የገንዘብም ሆነ የሞራል ድጋፍ ማግኘት ያልቻሉ ታዳጊ ወጣቶችን የሚደግፍ መርሐ ግብር ለመጀመር መሰናዳታቸውን ተናግረዋል። በመርሐ ግብሩ ለሚመረጡ ወጣቶች ድርጅቱ ያለ አንዳች ክፍያ ሀገር ቤት በሚገኙ ሰራተኞቹ በኩል የማፈላላግ ስራዎችን በነጻ ያከናውናል።