በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የምዕራብ ወለጋው ግድያና በዙሪያው ያሉ ንግግሮች


በኦሮምያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ውስጥ በሲቪሎች ላይ የተፈፀመውን ጥቃት እንደሚያወግዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልፀዋል።

ሰሞኑን በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በታጣቂዎች የተገደሉ ንፁሃን ዜጎችን ጉዳይ አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ማኅበራዊ ገፆቻቸው ላይ ባወጡት መልዕክት መንግሥታቸው በፈዴራልና በክልል በቅንጅት የአፀፋ እርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደረሰው ጥቃት ለሟቾች ቤተሰቦችና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰማቸውን ኀዘን በገለፁበት በዚህ መግለጫቸው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እርሳቸው “የጥፋት ኃይሎች” ላሏቸው ወጥመድ ላለመውደቅ “በማስተዋል እየተጓዘ በእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ከመንግሥት ጋር ተባብሮ ጥፋተኞችን ወደ ሕግ ለማቅረብና እንደዚህ ዓይነት ግድያዎችን ፈፅሞ እንዲቆሙ በትብብር ልንሠራ ይገባል።” ብለዋል።

በሌላ ዜና “በአማራ ላይ ለሚፈፀመው ግድያ ፌደራል መንግሥት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥ” ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር አሳስበዋል።

“ባለፉት ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ በተሠራው የጥላቻ ትርክት አማራ በሚኖርበት አካባቢ መገደል፣ መሳደድና መፈናቀል እየደረሰበት ነው” ያሉት አቶ አገኘሁ ይህንን ለማስቆም ከፌደራል እና ከክልል መንግሥታት ጋር በጋራ እየሠሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

“በተለይም ‘ኦነግ ሸኔ’ የተባለው ቡድን አማራን ነጥሎ በማጥቃት የሚታወቅ ነው። ‘የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ነፃ አውጭ’ ነኝ የሚል ቡድንም በአማራ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እያደረሰ ነው” ብለዋል።

ይህ ጉዳይ ካልተሻሻለ የሀገሪቱ ዜጎች ተቻችለው ለመኖር ለችግር የሚያዳርግ በመሆኑ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል።

በሌላ ዜና ምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ገንቤል ወረዳ ውስጥ ለተፈፀሙት የሰላማዊ ሰዎችን ህይወት ለቀጠፉ ጥቃቶች መንግሥት “ኦነግ ሸኔ” ብሎ የሚጠራውቸውን ታጣቂዎች ከስሷል። በጥቃቱ ሃያ ስምንት ሰው መገደሉንና ከአሥር በላይ ሰው መቁሰሉን ባለሥልጣናቱ አረጋግጠዋል።

መጠሪያው “የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት” እንደሆነ የሚናገረው ሸማቂ ቡድን “የምዕራብ ዕዝ አዛዥ ነኝ” ያሉት የቡድኑ መሪ መሮ ግን ክሡን አስተባብለዋል።

መሮ ለቪኦኤ ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

የምዕራብ ወለጋው ግድያና በዙሪያው ያሉ ንግግሮች
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:18 0:00


XS
SM
MD
LG