በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያዊው ህፃን ቲክ ቶክ ላይ በሚገኝ አደገኛ ውድድር ህይወቱ አደጋ ላይ ነው


ጆሽዋ ሀይለየሱስ
ጆሽዋ ሀይለየሱስ

በዩናይትድ ስቴትስ ኮሎራዶ ክፍለ-ግዛት፣ ዴንቨር ከተማ ነዋሪ የሆነ የ12 አመት ህፃን ቲክ ቶክ በተሰኘ የማህበራዊ ትስስር ገፅ ላይ የሚገኝ ትንፋሽን የመያዝ አደገኛ ውድድር ሲጫወት በደረሰበት አደጋ በህይወትና በሞት መካከል ይገኛል። ውድድሩ ተሳታፊዎች ትንፋሻቸውን በመያዝ ራሳቸውን እንዲስቱ የሚጠይቅ ሲሆን ህፃኑ ጆሽዋ ባደረገው ሙከራ ኦክስጅን ወደ ጭንቅላቱ እንዳይሄድ በማገዱ እራሱን ስቶ ተገኝቷል።

ኢትዮጵያዊው ህፃን ቲክ ቶክ ላይ በሚገኝ አደገኛ ውድድር ህይወቱ አደጋ ላይ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:10:57 0:00


የ12 አመቱ ጆሽዋ ሀይለየሱስ የ7ኛ ክፍል ተማሪና ለወላጆቹ ከመንትያ ወንድሙም በደቂቃ ቀድሞ የተወለደ የመጀመሪያ ልጅ ነው። ለወትሮው አብዝቶ ተጫዋች፣ ሙዚቃ የሚወድ፣ ምግብ ማብሰል የሚሞክርና በቤተክርስቲያን ተሳትፎ የነበረው ጆሽዋ አሁን በሞትና በህይወት መሀከል ከሆነ ሳምንት አስቆጠረ። ምክንያቱ ደግሞ ቲክ ቶክ በተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገፅ ላይ የተመለከተው ውድድር እንደሆነ ወላጅ እናቱ ፋሲካ እምሩ በሀዘን ትገልፃለች።

ጆሽዋን በመፀዳጃ ቤታቸው ወድቆ ያገኘው መንትያ ወንድሙ ካሌብ ሀይለየሱስ ነው። በድንጋጤ ግራ የተጋባችው እናቱና የአካባቢው ሰዎች ተጋግዘው ዴንቨር በሚገኝ ሆስፒታል ቢወስዱትም ጆሽዋ እስካሁን አልነቃም፣ ዶክተሮቹም ጆሽዋ በህይወት የሚቆይበት ጊዜ ረጅም እንዳልሆነ ለወላጆቹ ነግረዋቸዋል።

የልጃቸውን መዳን ከፈጣሪ ብቻ እየጠበቁ ላሉት ወላጆች በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት የደረሰባቸው አደጋ ግን ሊቋቋሙት ከሚችሉት በላይ ሆኖባቸዋል።

በብዙዎች ዘንድ ብላክ አውት ቻሌንጅ በመባል የሚታወቀው፣ ነገር ግን ከዚህ ቀደ ፓስ አውት ቻሌንጅ (ራስን የመሳት ውድድር) ፣ ዘ ጌም ኦፍ ቾኪንግ (እራስን ትንፋሽ የማሳጠር ጨዋታ) እና የመሳሰሉ ስሞች የነበሩት ውድድር -በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት ሰዎችን ለአደገኛ ውድድሮች የሚጋብዝ ጨዋታ ሲሆን የህፃናቶችን ህይወት አደጋ ላይ ሲጥል ጆሽዋ የመጀመሪያው አይደለም።

ከአሜሪካ የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1995 እስከ 2007 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ 82 ሰዎች በዚህ ውድድር ምክንያት ህይወታቸውን ሲያጡ አብዛኞቹ ከ11-16 አመት እድሜ ያላቸው ህፃናት ናቸው።

በጆሽዋ ላይ የደረሰው አደጋ ወላጆቹና ቤተሰቦችን ብቻ ሳይሆን መላውን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ያስደነገጠና እጅግ ያሳሰበ ክስተት ነው። ለቤተሰቡ የቅርብ ጓደኛ የሆነችውና የአስር አመት ሴትና የ7 አመት ወንድ ልጆች ያሏት ቤዛ ክንፈ እስካሁን በጆሽዋ ላይ የደረሰውን ለማመን እንደከበዳት ትናገራለች።

ቤዛ በማህበራዊ ሚዲያ አማካንነት በጆሽዋ ላይ የደረሰው አደጋ ለሌሎች ወላጆች የማንቂያ ደውል እንደሆነም ትገልፃለች። በተለይ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ልጆች ለትምህርትም ሆነ ለመዝናኛ አብዛኛውን ሰዓታቸውን በኢንተርኔት ላይ የሚያጠፉ በመሆናቸው ጊዜያቸውን መገደብ፣ ምን እንደሚያዩ መከታተልና፣ በየጊዜው ሀሳባቸውን ማወቅ ከምንግዜውም በላይ አስፈላጊ ነው ትላለች።

እንደ ፌስቡክ፣ ትዊተርና ጉግል የመሳሰሉ ግዙፍ የማህበራዊ ትስስር ኩባንያዎች በድህረ-ገፆቻቸው ላይ የሚያሰራጩዋቸው መረጃዎች በህብረተሰቡ ላይ እያደረሱ ያለውን ጥፋት ለመቀነስ የአሜሪካ ምክርቤቶች ርብርብ ላይ ናቸው። ባለፈው ሳምንት የኩባንያዎቹ ባለቤቶች በምክር ቤቱ ቀርበው ቃላቸውን እንዲሰጡ በተድረገበት ወቅትም የሪፐብሊካን ተወካይዋ ካቲ ማክሞሪስ ሮጀርስ ኩባንያዎቹ ለልጆች አድጋ እየሆኑ መምጣታቸውን አስረግጠው ተናግረዋል።

ቤዛም በቀጣይ ወላጆች ማድረግ ያለባቸው ነገር ልጆቻቸውን በማህበራዊ ሚዲያዎች ከሚሰራጩ አደገኛ መረጃዎች የሚጠብቅና የሚከልል ህግ እንዲወጣ መንግስታት ላይ ግፊት ማድረግ ነው ትላለች።

ያ እስከሚሆን ግን ልጆችን የመጠበቅ ሀላፊነት አሁንም ወላጆች ጋር ይወድቃል። ይህ ሀላፊነት ታዲያ ምን መምሰል አለበት ስንል ለበርካታ አመታት አትላንታ ውስጥ መምህራንን በማሰልጠንና በልጆች ዙሪያ በመስራት የሚታወቁትን ወይዝሮ ብሌን ተክሉን ጠይቀናቸዋል።

ወይዘሮ ብሌን አክለው በወላጆችና በልጆች መሀከል ግልፅ የሆነ ግንኙነት መኖር መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑንም ያሰምሩበታል።

የጆሽዋ በህክምና መዳን ተስፋ እንደሌለው የተነገራቸው ወላጆች -ፋሲካና ሀይለየሱስ - ግን በእምነታቸው ተስፋ አልቆረጡም። በርካታ ኢትዮጵያውያንም ጆሽዋ በተኛበት የሆስፒታል ቅጥር ግቢና በያሉበት በፀሎትና በገንዘብ እያገዟቸው ነው። ጎን ለጎንም በልጃቸው የደረሰው በሌሎች እንዳይደርስ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲጠብቁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

XS
SM
MD
LG