በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የጸረ ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ ውል ሃሳብ ድጋፍ አግኝቷል


የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም
የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም

ወደፊት የሚከሰቱ ዓለም አቀፍ አጣዳፊ የጤና አደጋዎችን በተሻለ መንገድ ለመዋጋት የሚረዳ ዓለም አቀፍ ጸረ ወረርሽኝ ውል እንዲፈረም የቀረበውን ሃሳብ የአውሮፓ ህብረት የዓለም የጤና ድርጅት እና የሃያ ሦስት ሃገሮች መሪዎች እንደሚደግፉት አስታውቋል።

የዓለም መሪዎቹ የዓለም የጤና ድርጅት እና የአውሮፓ ህብረት ፊርማቸውን ያኖሩበት አስተያየት ዛሬ በበርካታ የዜና ማሰራጫዎች ታትሞ ወጥቷል። ዩናይትድ ስቴትስ ቻይና እና ሩስያ ግን የሉበትም።

ክትባቶች፣ መድሃኒቶች እና የበሽታ መመርመሪያ አቅርቦቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍትሃዊ ተደራሽ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ውል እንዲፈረም የሚለውን ሃሳብ ባለፈው ህዳር ወር በተካሄደው የጂ ሃያ መሪዎች ጉባዔ ላይ ያነሱት የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዚዳንት ሻርል ሚሼል ነበሩ። ከዚያ በማስከተል የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ሃሳቡን እንደደገፉ ይታወሳል።

የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዚዳንት ሚሼል እና የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ከብረስልስ እና ከጄኔቫ በጋራ በሰጡት መግለጫ የዓለም አቀፍ ውሉን አስፈላጊነት ዘርዝረው አስረድተዋል።

ሻርል ሚሼል የዓለም አቀፍ ውሉን አስፈላጊነት በድህረ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት፣ የዓለም መሪዎች በአንድነት ከመሰረቱት ዓለም አቀፍ ትብብር ጋር ተመሳሳይ መሆኑን አውስተዋል። እንዲህ ያለውን ውል ስንዋዋል አሉ ሚ ሼል የሰው ልጆች፥ የእንሥሳት ጤናና የምድራችን ደህንነት የተቆራኘ በመሆኑ በጋራ ኃላፊነት ግልጽነት እና ትብብር መያዝ አስፈላጊ መሆኑን ያሳይልናል ብለዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በበኩላቸው ዓለም አቀፍ ውል መፈረሙ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ላሳየን ክፍተቶች መላ እንድንፈልግ እና ዓለም አቀፍ የጤና ጥበቃ ደንቦች ሥራ ላይ መዋላቸውን በተጠናከረ መንገድ እንዲከበሩ ለማድረግ ይረዳል ብለዋል። ወረርሺኞችን በመከላከልና በመዋጋት ረገድ የተቀናጀ ሥራ ለመስራት ያግዛል ብለዋል።

XS
SM
MD
LG