በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኦክስፈርድና አስትራዜኒካ የኮቪድ ክትባት ውዝግብ


የመድሃኒት ኩባኒያው የኮቪድ-19 ክትባቱን ፍቱንነት አጋንኖ በሰጠው መግለጫ ላይ ያቀረበው የክትባቱ ሙከራ መረጃ ጊዜው ያለፈበት መረጃም ሳይታከልበት አልቀረም ሲል አንድ ዋና የዩናይትድ ስቴትስ የመድሃኒት ተቆጣጣሪ አካል ስጋቱን ገልጿል።

አስትራዜኒካ ትናንት ሰኞ ባወጣው መግለጫ ክትባቱ "በኮቪድ-19 ምክንያት ሆስፒታል እስከመግባት በሚያደርስ ደረጃ በጽኑ መታመምን መቶ በመቶ እንደሚከላከል ብዛት ያላቸው ተሳታፊዎች ያካተቱ የክትባቱ የመጨረሻ ምዕራፍ ሙከራዎች አረጋግጠዋል ብሏል።

ይህንኑ ተከትሎ የዩናይትድ ስቴትስ ብሄራዊ የአለርጂ እና የተላላፊ በሽታዎች ተቋም የምምክር ክንፍ የሆነው የአሃዛዊ መረጃዎች እና የደህንነት ቁጥጥር ቦርድ ዛሬ ማለዳ በጉዳዩ ላይ መግለጫ አውጥቷል። ቦርዱ በመግለጫው የብሪታንያና የስዊድኑ የምድሃኒት ኩባኒያ ስለክትባቱ ፍቱንነት ያልተሟላ ግንዛቤ ሊሰጥ የሚችል መረጃ ሳይኖርበት አይቀርም ብሏል።

አስትራዜኒካ በትናንቱ መግለጫው ስለጸረ ኮቪድ ክትባቱ ውጤታማነት እና ለጎን የጤና ጠንቅ ስጋት የማይደቅን ስለመሆኑ ከድምዳሜ የደረሰው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከሰላሳ ሺህ በላይ ሰዎች ባሳተፈው ሙከራ ውጤት ላይ ተመርኩዞ መሆኑን ነው ያስታወቀው።

የዩናይትድ ስቴትሱ ነጻው አማካሪ ቦርድ በበኩሉ ስለክትባቱ ፍቱንነት ባፋጣኝ ትክክለኛው እና ወቅቱን የጠበቀ መረጃ መስጠት ይቻል ዘንድ መረጃዎቹን አብረናችሁ ለመገምገም ዝግጁ ነን ሲል አስታውቋል።

በርካታ የአውሮፓ ሃገሮች ክትባቱ የደም መርጋት ያስከትላል ያሉ ሪፖርቶችን ተከትሎ ክትባቱ ለዜጎቻቸው እንዳይሰጥ ማድረጋቸው ይታወሳል። የአውሮፓ የመድሃኒቶች ጉዳይ ኢጄንሲም ክትባቱ የደህንነት ስጋት ባጠቃላዩ የደም መርጋት ስጋትም ጭምር የማይደቅን እንደሆነ ማስታወቁ የሚዘነጋ እየይደለም።

የዓለም የጤና ድርጅት በበኩሉ ክትባቱ ሊያስከትል ከሚችለው የጎን ስጋት ይልቅ ጠቀሚታው እንደሚያመዝን ገልፆ፣ ክትባቱ የተለወጡ የኮሮናቫይረስ ዓይነቶችን ለመከላከል መሰጠቱ እንዲቀጥል መክሯል።

XS
SM
MD
LG