በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአስትራዜኒካ ክትባት የጎንዮሽ የጤና ስጋት እንዳላሳየ ተገለጸ


የመድሃኒት አምራች ኩባኒያው አስትራዜኒካ የኮቪድ-19 ክትባት በበሽታው ሆስፒታል ለመግባት በሚያደርስ ደረጃ በጽኑ መታመምን መቶ በመቶ የመከላከል ፍቱንነት ያለው መሆኑን አስታወቀ። ክትባቱ የበሽታውን ምልክቶች በሚያሳይ ደረጃ መታመምን በመከላከል ረገድ ደግሞ ሰባ ዘጠኝ ከመቶ ፍቱንነት ያለው መሆኑ ተገልጿል።

ኩባኒያው ከዚህ የክትባቱ ግምገማ ላይ የደረሰው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ 32ሽህ 449 ሰዎች ባሳተፈ ሙከራ ውጤት ላይ ተመርኩዞ መሆኑን ገልጾ፣ ክትባቱ ምንም ዓይነት የጎንዮሽ የጤና ስጋት እንዳላሳየ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በቅርቡ በርከት ያሉ የአውሮፓ ሃገሮች ክትባቱን በወሰዱ ሰዎች ላይ የደም መርጋት ተከስቷል ብለው የወጡ ሪፖርቶችን ተከትሎ ክትባቱ ለህዝቦቻቸው እንዳይሰጥ መከልከላቸው አይዘነጋም፣ ሆኖም የመድሃኒቶችን ደህንነት የሚቆጣጠረው የአውሮፓ የመድሃኒት ድርጅት ኢኤምኤ ክትባቱ የጎንዮሽ ጠንቅ ስጋት የማያስከትል እና በአጠቃላዩም በደም መርጋት ረገድ ስጋት የማይደቅን መሆኑ አስታውቋል።

ይህንኑ ተከትሎ የዓለም የጤና ድርጅት ክትባቱ ከሚያስከትለው ስጋት የሚሰጠው ጥቅም እንደሚያመዝን አስታውቆ ልውጦቹን የኮሮናቫይረስ ዓይነቶች ለመከላከል ጥቅም ላይ እንዲውል ምክረ ሃሳብ ሰጥቷል።

በሌላ በኩል ደቡብ አፍሪካ የአስትራዜኔካው ክትባት በሀገርዋ የተቀሰቀሰውን የኮሮናቫይረስ ልውጥ ዝርያ አይከላከልም በሚል ስጋት ህዝቧን በሱ መከተብ አቁማለች። የክትባቱን ክምችቷን ቢያንስ አንድ ሚሊዮን የሚሆነውን ለአፍሪካ ህብረት ሸጣዋለች። የአፍሪካ ህብረት የገዛውን ክትባት ለአስራ አራት የአህጉሪቱ ሃገሮች እንደሚያከፋፍል ተገልጿል።

XS
SM
MD
LG