በቀድሞው የዩናይትድ ስቴስት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ላይ የቀረበውን ታሪካዊ እና ሁለተኛውን ክስ ለማድመጥ የዩናይትድ ስቴትስ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ዛሬ ዳኝነት ይቀመጣል። ትራምፕ የተከሰሱት፤ በኢሌክቶራል ኮሌጅ ድምፅ (ባለ ድምፅ ተወካይ መራጮች ድምፅ) የ2020 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ መሆናቸው የተነገረውን ዴሞክራቱ ጆ ባይደን ውጤትን ማረገጫ ለመስጠት ከአንድ ወር በፊት በምክር ቤቱ የተሰበሰቡ እንደራሴዎችን እንዲሞግቷቸው አሰማርተዋል በሚል ነው።
የተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ 800 የሚሆኑ ደጋፊዎች፣ የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት ሕንፃን በመውረር፣ በርና መስኮቶችን ሰባብረው ወደ ውስጥ በመግባት የአንዳንድ የምክር ቤት አባላት ቢሮዎችን ዘረፈዋል። ከምክር ቤቱ ጠባቂ ፖሊሶች ጋርም ተጋጭተዋል። አንድ የምክር ቤቱ የፖሊስ ባልደረባን ጨምሮ አምስት ሰዎች በአመፁ ወቅት ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ክሱ እንዴት ተጀመረ?
ዓመፁ ከተደረገበት ታኅሣሥ 28 አንድ ሳምንት በኋላ ድምፃቸውን ከሰጡት 429 የምክር ቤቱ እንደራሴዎች ውስጥ 232ቱ ትረምፕ መከሰስ አለባቸው ሲሉ ውሳኔ አሳለፉ። ከእነዚህ ውስጥ 222ቱ ዴሞክራቶች ሲሆኑ 10 ሪፐብሊካኖችም እንዲከሰሱ ድምፅ ሰጥተዋል።
እንደራሴዎቹ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ በሕገወጥ መንገድ ሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲሉ ምርጫው ተጭበርብሯል በማለት ደጋፊዎቻቸው የምክር ቤቱን ሕንፃ ወረው ጥቃት እንዲፈጽሙ አድርገዋል ሲሉ የቀረበውን ይህንን የክስ አንቀፅም (Impeachment) ጥር 17/2013 ዓ.ም በይፋ ለመወሰኛ ምክር ቤቱ አስገብተዋል። ቃለ መሃላም ፈፅመዋል። ትረምፕ በወቅቱ ምርጫው መጭበርበሩን ሲገልፁ “በፍፁም ተስፋ አንቆርጥም ውጤቱንም መቼውንም አንቀበልም” ብለው ነበር።
ታኅሣሥ 28/2013 ዓ.ም ቀን ከተፈፀመው ዓመጽ ጋር በተያያዘ በመላ አርሪቱ 160 ሰዎች ታስረዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ በምርመራ ላይ ናቸው።ዶናልድ ትራምፕ በደቦ የተደራጁ ጥቃት አድራሾች ምክር ቤቱን እንዲወሩ በማነሳሳት እጃቸው እንዳለበትም ተጠቅሷል።በዋሽንግተን የሚገኙ ህንፃዎች ላይ ፍንዳታ በማድረስ ማሴር ወንጀል የተጠረጠረው የካሊፎኒያ ተወላጅ ደግሞ ምርመራ እየካሄደበት ነው። የአገር ውስጥ ደህንነት መምሪያ በአገር ውስጥ ጽንፈኞች ስለሚደርሱ ጉዳቶችም ማስጠንቀቂያ አውጥቷል።
ትረምፕ በምክር ቤቱ የተነሳውን የአመፅ ድርጊት ተከትሎ የዩናይትድ ስቴትስ ሕገመንግሥት 25ኛ ማሻሻያ በሚያዘው መሠረት፤ “ከሥልጣንም መወገድ አለባቸው” ከሚሉ የዴሞክራቲክና ሪፐርብሊካን ፓርቲ አባላት ከፍተኛ ግፊት እየደረሰባቸውም ነበር፡፡
የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፐሎሲ ትረምፕ መከሰስ እንዳለባቸው በወተወቱበት ጊዜ፤ “ከዚህ በኋላ የትኛውም ፕሬዚዳንት ዓመፅ ማነሳሳት እንደማይቻል መገንዘብ እንዲችል ትረምፕ መከሰስ እና ጥፋተኛ መባል አለባቸው” ብለው ነበር።
ናንሲ ፐሎሲ ትራምፕ መከሰስ እንዳለባቸው አብዝተው መወትወት ከጀመሩ እና ዐመፁ ከተከሰተ ከአንድ ሳምንት በኋላ ትረምፕ ገና በሥልጣን ላይ እያሉ ነበር እንዲከሰሱና ከሥልጣን እዲወርዱ ጥያቄው መቅረብ የጀመረው። የዚህ ክስ ሂደት ሳይጠናቀቅ የቀድሞው ፕሬዚዳንት የምርጫውን ውጤት ተቀብለው ሥልጣናቸውን አስረክበው ነጩን ቤተ መንግሥት ቢለቁም ክሱ ግን አሁም ቀጥሏል። የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ትረምፕን ከሥልጣን ለማውረድ እና እንዲከሰሱ ለማድረግ አብላጫዎቹም ድምጽ ሰጥተዋል።
አንዳንድ ከፍተኛ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላትም ትራምፕ በሁከት ውስጥ ሚና እንደነበራቸው አምነው ቃላቸውን ሰጥተዋል። በምክር ቤቱ የአናሳው መሪ ሚች ማክኔል ፤ “አመፀኞቹ ውሸት ተግተዋ። በፕሬዚዳንቱ እና ሥልጣን ባላቸው ሌሎች ሰዎች የተነሳሱ ናቸው።” ሲሉም ድርጊቱ አጠንክረው ኮንነውት ነበር።
በ50 ዴሞክራትና በ50 ሪፐብሊካን በአጠቃላይ 100 አባላት ያሉት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ክሱን ለማድመጥ ዛሬ ይሰየማሉ።
“ትረምፕ ጥፋተኛ ናቸው” የሚለውን ውሳኔ ለማፅደቀ የፍፁም አብላጫ ሁለት ሦስተኛ የሆነ ድምፅ መገኘት አለበት። በ50 ዴሞክራትና በ50 ሪፐብሊካን በአጠቃላይ 100 አባላት ያሉት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ክሱን ለማድመጥ ዛሬ ይሰየማሉ። እንዲህ ያለ የክስ አንቀፅ የመስማት ሂደት በሚካሄድበት ግዜም ፕሬዚዳንቱ የተለየ ሁኔታ ይኖራቸዋል። አብዛኞቹ እንደራሴዎች ታኅሣሥ 28/2013 ዓ.ም አመፁ ሲነሳ የዐይን እማኞች ነበሩ። ለደህንነታቸው ሲሉም ከምክር ቤቱ ውስጥ ወጥተው ነበር። በዚህ ክስ ዴሞክራቶች ሙሉ በሙሉ ትረምፕ ጥፋተኛና ናቸው ብለው ይወስናሉ ተብሎ ቢገመት፤ ውሳኔውን ለማጽደቅ 17 ሪፐብሊካኖች ድምፅ መስጠት ይኖርባቸዋል።
ከአንድ ዓመት በፊት ትረምፕ፤ ለዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ስልክ ደውለው በፖለቲካ ተቀናቃኛቸውና በመጭው ምርጫም ሊጋፈጧቸው በሚችሉ ባላንጣቸው የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ልጅ ኸንተር ባይደን ላይ ምርመራ እንዲያካሂዱ የመጠየቃቸው ወሬ ከወጣ በኋላ፤ የፕሬዚዳንቱን ቢሮ ኃይል እና አቅም ለራሳቸው የፖለቲካ ጥቅም ጉዳይ ያለ አግባብ ተጠቅመውበታል የሚል የመጀመሪያ ክስ ቀርቦባቸው ነበር።
በወቅቱ የጥፋተኝነት ውሳኔ ባይተላለፍባቸውም አሁን በድጋሚ ተከሰዋል። የዚህ ክስ ውጤት ምንም ሆነ ምን ትረምፕ በዩናይትድ ስቴት ታሪክ ውስጥ ሁለት ግዜ ክስ የቀረበባቸው ብቸኛ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ። ጥፋተኛ ከተባሉም ከዚህ በኋላ የትኛውንም የፌደራል መንግሥት ሥልጣን እንዳይዙ ይደረጋሉ።
በቺካጎ ዩኒቨርስቲ መመሕር የሆኑት አዙ ሃቅ ስለ ድምፅ አሰጣጡ አስቀድመው ሲገምቱ፤ “በእንደራሴዎቹ ምክር ቤት ውስጥ ያሉት ሪፐብሊካን የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተሳታፊነት ወይም በአጥፊነት በሪፐብሊካን ፖለቲካ ውስጥ ሊጫወቱት ስለሚችሉት ሚና ያስባሉ። ድምፃቸውን የሚሰጡትም የወደፊቱ ሪፐብሊካን ፓርቲ ሊሆን ይችላል ብለው በገመቱት መሰረት ነው።” ይላሉ።
ዲሞክራቶች ከሪፐብሊካኖች የይከሰሱ ይሁንታን የሚገልፅ በቂ ድምጽ አለመኖሩ ያሳስባቸዋል ፣ እናም የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ የዳኝነት ሂደት በፕሬዚዳንት ጆ ቢደን የመጀመሪያዎቹ የሥልጣን ሣምንታት ላይ እክል ይፈጥራል የሚል ስጋት አላቸው።
የመወሰኛ ምክር ቤቱ ብዙኃን መሪ ናቸው ቻክ ሹመር፤ “ምንም መጠራጠር አያስፈልግም። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ትረምፕ ላይ የቀረበባቸው ማስረጃ ሃገሪቱ በምታየው ደረጃ ደምቆ ይቀርባል። እያንዳንዱም ሰዎ ያየዋል።” ሲሉ ተናግረዋል።
በብሩኪንግስ ተቋም አጥኒዋ ኤአኒ ካማርክ፤ “ከዚህ ቀደም የተወሰኑት ፕሬዚዳንቶች ቢከሰሱም ማንም ተፈርዶበት የሚያውቅ ግን የለም። ስለዚህ በዚህ መልኩ ታሪካዊ ነው። አንድ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሕጋዊ ነገሮችን ሁሉ አሟጦ ሲጨርስ ሥልጣን ላይ ለመቆየት አድማ ለማድረግ መሞከሩ ታሪካዊ ያደርገዋል።” ብለዋል።
ትረምፕ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ከዴሞክራት ቀርቦላቸው የነበረውን ጥሪ አልተቀበሉትም። ስለዚህ በክስ የመስማት ሂደቱ ላይ ይገኛሉ ተብሎ አይጠበቅም።
(በቪኦኤ የምክር ቤት ዘጋቢ ካትሪን ጊይብሰን የተጠናቀረውን ዘገባ ጽዮን ግርማ ወደ አማርኛ መልሳዋለች)