በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሰብዓዊ ረድኤት ሠራተኞች ትግራይ ለመሄድ ፈቃድ እየጠበቁ መሆኑን ዩ.ኤን አስታወቀ


በሱዳን ጋደሪፍ የስደተኛ ጣቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን
በሱዳን ጋደሪፍ የስደተኛ ጣቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን

ሰማኒያ የሚሆኑ የተባበሩት መንግሥታት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅት ሠራተኞች ወደ ትግራይ ክልል ለመጓዝ የሚያስችላቸውን ፈቃድ ለማግኘት አዲስ አበባ ሆነው ሲጠባበቁ አንድ ወር እንዳለፋቸው ድርጅቱ አስታውቋል። በተጨማሪም በክልሉ ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን በዚያ የሚገኙ ባልደረቦቻቸው እየገለፁላቸው መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፈኒ ዱጃሪክ የአገራትን ሁኔታ በተመለከተ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታወቁ።

ቃል አቀባዩ በዚሁ ማብራሪያቸው ላይ እንደጠቀሱት፤ በደህንነት ስጋት እና በቢሮክራሲ ችግር ምክኒያት ትግራይ ክልል ውስጥ እርዳታ ለሚፈልጉ ሰዎች በበቂ ሁኔታ ተደራሽ መሆን እንዳልተቻለ ገልፀው፤ ወደ ቦታው ገብቶ እርዳታውን ለመለገስ የተሰጠው ፈቃድ ውስን መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት እየተሰጡ ያሉ ድጋፎች አጠቃላይ ከሚያስፈልገው ጋር ሲነፃፃር በቂ አለመሆኑን የገለፁት ቃል አቀባዩ ፤ ምንም እንኳን ድጋፋችንን ለማሳደግ ብንችልም አሁንም ከመቀሌ ወደ ሽሬ በሚወስደው መንገድ ላይ በሚገኙ ሁለት የስደተኛ ካምፖች ውስጥ ያሉ ሰዎችን ለመርዳት ውስንነት እንዳለባቸው አስታውቋዋል።

ይህም ሆኖ በአሁኑ ሰዓት በትግራይ ደቡባዊ ክፍል በሚገኙ ማይ-አይኒ እና አዲ ሃሩሽ በተሰኙ ሁለት የስደተኛ መጠለያ ውስጥ ለሚገኙ 250 ሺሕ ሰዎች ለሁለት ወራት የሚሆናቸውን ምግብ ማከፋፈል መቻሉን ገልፀዋል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የሕክምና እቃዎችም ተገዝተው መላካቸውን ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል።

አያይዘውም ትግራይ እና በአማራ ክልል የሚፈፀሙ ጾታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል እና ጥቃቱ ለደረሰባቸው ተጎጂዎችም እገዛ ለማድረግ አጋሮቻቸው እየረዷቸው መሆኑን ገልፀዋል። የሰብዓዊ እርዳታውን ለማድረስ ለእርዳታ ሠራተኞች የኢትዮጵያ መንግሥት ያልተገደበ ፈቃድ እንዲሰጥ ጥያቄ ማቅረባቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

XS
SM
MD
LG