በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ትምህርት በዩቲዩብ


የሁለተኛ ደረጃና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ብቃት ለማሻሻል የሚረዳ 'ሀ-ሁ ክላስ' የተሰኘ የዩቲዩብ ቻናል
የሁለተኛ ደረጃና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ብቃት ለማሻሻል የሚረዳ 'ሀ-ሁ ክላስ' የተሰኘ የዩቲዩብ ቻናል

የሁለተኛ ደረጃና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ብቃት ለማሻሻል በዩቲዮብ አማካኝነት የድጋፍ ትምህርቶችን እያዘጋጁ ለተማሪዎች የሚያቀርቡ የጅጅጋ ዩንቨርስቲ መምህር እንግዳ አርገን ጋብዘናል። እንግዳችን ዶክተር አያሌው ንጉሴ ይሰኛሉ፣ በትምህርት ጥራትና ከዛ ጋር አያይዘው በሚሰሯቸው ስራዎች ዙሪያ አነጋግረናቸዋል።

ትምህርት በዩቲዩብ
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:51 0:00

ዶክተር አያሌው ንጉሴ ላለፉት 13 አመታት በጅጅጋ ዩንቨርስቲ የማይክሮ ባዮሎጂ መምህርና ተመራማሪ ሆነው፣ በተጨማሪም ከክፍል መምህርነት አንስቶ እስከ ኮሌጅ አመራር ሆነው ሲያገለግሉ በስፋት ያስተዋሉትና እጅጉን የሚያሳስባቸው የተማሪዎች ብቃት ማነስ ነው።

ለዚህ የተማሪዎች ብቃት ማነስ በዋናነት አስተዋፅኦ የሚያደርገው በኢትዮጵያ በየጊዜው እያሽቆለቆለ የሚሄደው የትምህርት ጥራት መሆኑን ዶክተር አያሌው ያሰምሩበታል። ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ በከፍተኛ ቁጥር የተስፋፉት የትምህርት ተቋማት በቂ ዝግጅት ሳይኖራቸው፣ ቁሳቁስ ሳይሟላላቸውና በበቂ ሁኔታ የሰለጠኑ መምህራን ሳያገኙ የሚያስተምሯቸው ተማሪዎች በትምህርት ምዘና ወቅት የሚያመጡት ውጤት እጅግ ዝቅተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ አገሪቱ የምታገኘው አምራች ሀይል ላይም ከፍተኛ ተፅእኖ እያደረገ ነው።

በበቂ ሁኔታ ያልሰለጠኑ መምህራን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥም እንደሚገኙ ዶክተር አያሌው ያስረዳሉ።

ሌላው በከፍተኛ ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውና ለትምህርት ጥራቱ ማሽቆልቆል የራሱን ሚና የሚጫወተው ደግሞ በእንግሊዘኛ plagiarism ተብሎ የሚጠራው፣ የመመሪቂያ ስራዎቻቸውንም ሆነ ሌሎች የጥናት ፅሁፎቻቸውን ከሰውን ሀሳብ በመውስድ ወይም በመስረቅ የሚሰሩ ተማሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨረ መምጣቱ ነው። በተለይ ከኢንተርኔት መስፋፋት ጋር ተያይዞ፣ ይህ ችግር እየተባባሰ መምጣቱን ዶክተር አያሌው ያስረዳሉ።

እነዚህና በትምህርት ዙሪያ የሚታዩ ሌሎች ተደራራቢ ችግሮች ናቸው ዶክተር አያሌውን 'ሀ-ሁ ክላስ' የተሰኘ የዩቲዩብ ቻናል በመክፈት፣ ማህበራዊ ሚዲያን ለተማሪዎች የትምህርት ድጋፍ ለመስጠት እንዲጠቅሙ ያነሳሳቸው። ላለፉት ሁለት ወራትም ከሌሎች በጎ ፈቃደኛ መምህራን ጋር በመሆን ከ 9ኛ-12ኛ ክፍል ላሉ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችና ለዩንቨርስቲ ተማሪዎች ተከታታይ ትምህርቶችን እየሰጡ ይገኛሉ።

ዶክተር አያሌው ሀ-ሁ ክላስ የተሰኘውን የዩቲዩብ ቻናል የጀመሩበት ሌላም ምክንያት አላቸው። በተለይ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ተማሪዎችና መምህራን ከትምህርት ርቀው በማህበርዊ ድህረገፆች ላይ የሚያጠፉት ጊዜ እያሳሰባቸው በመምጣቱ የዩቲዩብ ቻናሉ የትምህርት ባለሙያዎች ጊዜአቸውን ወደ ሙያቸው እንዲመልሱ ለማድረግ እንደሚረዳ ዶክተር አያሌው ያስረዳሉ።

የዩቲዩብ አስተምሮ ለኢትዮጵያ አዲስ ይሁን እንጂ በአለም ላይ ግን ተፈላጊ እየሆነ የመጣ የመማሪያ ዘዴ ሆኗል። ኢትዮጵያ ውስጥም ወደፊት የመለመድ እና ከክፍል ትምህርት ጎን ለጎን ጥሩ አጋዥ የመሆን ተስፋ እንዳለው ዶክተር አያሌው ባደረጉት አነስተኛ ጥናት አረጋግጠናል ይላሉ። ስለሆነም የሀ-ሁ ክላስ ጅማሬ በትምህርት ቢሮዎችና የትምህርት ተቋማት ከታገዘ ለትምህርት ጥራት መሻሻል አንድ አስተዋፅኦ ሊያደርግ ይችላል።

XS
SM
MD
LG