በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሥነ-ጥበብ ማህበረሰብን ማከም ይቻላል - የሥነ-ጥበብ ባለሙያ ዮናስ ሀይሉ


በሥነ-ጥበብ ማህበረሰብን ማከም ይቻላል - የሥነ-ጥበብ ባለሙያ ዮናስ ሀይሉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:38 0:00

ስደት በኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ እንዴት ይገለፃል የሚል አውደ ርዕይ በጀርመን ባህል ማእከልና በአለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት አማካኝነት ተዘጋጅቶ ነበር። በድህረ ገፅ አማካኝነት በኢትዮጵያና በጀርመን በታየው በዚህ አውደ ርዕይ ላይ ስራዎቹን ያቀረበው ዮናስ ሀይሉ ሥነ-ጥበብ ማህበራዊ እውነታዎችን ለመነጋገርና የጋራ እሴቶችን ለማጎልበት ትልቅ ሚና አለው ይላል።

ስደት ከሰው ልጆች ታሪክ ጋር አብሮ በቁርኝት የኖረ ነው። በተለይ ግን በ21ኛው ክፍለ ዘመን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምክንያቶች ስደት የአለማችን ቀዳሚ መነጋገሪያ ከሆኑ አጀንዳዎች መካከል አንዱ ሆኗል። ይህ እውነታ የሥነ ጥበብ ባለሙያና መምህር ለሆነው ዮናስ ሀይሉ፣ ስደተኛ ማነው? አሳዳጅስ? የሚለውን ጥያቄ እንዲጠይቅና፣ በጥናት የተደገፈ የጥበብ ስራውን በአውደ ርዕይ እንዲያቀርብ መነሻ እንደሆኑት ይናልገራል።

ዮናስ የሥነ-ጥበብ ስራዎቹን ያቀረበው ዘመናዊ ዲጂታል የፎቶ መተግበሪያዎችን ከባህላዊው የሥነ-ቅብ ስራ ጋር በማደበላለቅ ነው። በስራው ለማሳየት የሞከራቸው ታሪኮችም ለሰዓታት ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸውን ስምንት የእውነተኛ ባለታሪኮችን ህይወት የሚያስቃኝ ነው። ከባለታሪኮቹ መካከል ከእናቷ ጋር ከየመን ተሰዳ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ስትለምን ያገኛት የስምንት አመት የመናዊት እና በአሜሪካን አገር የሚኖረው ወጣት ይገኙበታል።

በርካታ አፍሪካውያን ወደ አውሮፓ የሚያደርጉት የሞት ሽረት ትግል የሞላበት ስደት፣ በስደት በሄዱበት ሀገር የሚገጥማቸው እንግልትና የኑሮ ውጣ ውረድ የስደት ክፉ ገፅታዎች ጎልተው እንዲወጡ ቢያደርጓቸውም ዮናስ በስራዎቹ ስደት ለባህል ልውውጥ፣ እድገት እና አብሮ መኖር ያደረገውን አስተዋጾኦም ለማሳየት እንደሞከረ ይናገራል።

ዮናስ ከአለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት በ2002 ዓ.ም. ከተመረቀ በኃላ ከ 35 በላይ አውደ ርዕዮችን በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ አሳይቷል። በአሜሪካ፣ በአውሮፓና በእስያ የተለያዩ ሀገሮች ላይ የተደረጉ ውድድሮችን ከማሸነፉና የባህል ልውውጦችን ከማድረጉ በተጨማሪ በጣሊያ፣ ኳታር፣ ባህሬን፣ አሜሪካና ብራዚል በሚገኙ ሙዚየሞች ስራዎቹ ተቀምጠዋል።

ሥነ-ጥበብ የተለያዩ ማንነቶች፣ የእውቀት ደረጃና እውነቶች ያሏቸውን ማህበረሰቦች የማስተሳሰር ሀይል አለው የሚለው ዮናስ በስራዎቹ በአብዛኛው እነዚህን የጋራ እሴቶች የሚያንፀባርቁ ናቸው።

የማንነት ጥያቄዎች በማህበረሰቦች መሃል የግጭቶች መንስኤ ከመሆን አልፈው ለብዙ ሰዎች ህይወት መጥፋትና ለሚሊዮኖች መፈናቀል ምክንያት በሆነበት በአሁኑ ወቅት፣ ዮናስ ስነ-ጥበብ ህብረተሰብን የማከምና የመፈውስ አቅም እንዳለው ይናገራል።

ዮናስ ከሥነ-ጥበብ ባለሙያነቱና ከመምህርነቱ ባሻገር የማህበራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች አቀንቃኝም ነው። በቅርቡም ኳንዛ የተሰኘ የአፍሪካ ፍልስፍና ሀሳቦችን የያዘ በራስ ማየት፣ ስነጥበባዊ ፈጠራ፣ እምነት፣ በራስ መተማመንና አብሮ መኖር በሚሉ ሀሳቦች ዙሪያ የሥነ-ጥበብ አውደ ርዕይና ውይይት ያካሂዳል። ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተያያዙ ሀሳቦች የሚቀእርቡበት ከእናት ተፈጥሮ ጋር የሚደረግ ቃለ-ምልልስ የሚል አውደ ርዕይ ላይም ስራዎቹን ያቀርባል።

XS
SM
MD
LG