በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በወር አበባ ንጽህና መጠበቂያዎች ላይ የቀረጥ ማሻሻያ ቢደረግም አቅርቦቱን ለማሻሻል ብዙ ስራ ይጠይቃል


የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ምርቶች
የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ምርቶች

የገንዘብ ሚኒስቴር የንፅህና መጠበቂያ ምርቶች ላይ ቀረጥ ላይ ማሻሻያ ማድረጉን በዚህ ሳምንት አስታውቋል። በተለይም የሴቶች የወር አበባ መጠበቂያ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች፣ ከውጪ የሚያስገቧቸው ጥሬ እቃዎች ከቀረጥ ነፃ መሆናቸውን ታውቋል። የቀረጥ ማሻሻያው በተለይ የሴት ተማሪዎችን ህይወት ሊቀይር የሚችል መሆኑ ቢገለፅም ይህ መሻሻል እንዲመጣ ሀገር አቀፍ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የቆየው 'ጀግኒት' የተሰኘ ንቅናቄ ተፈፃሚነቱን ለማረጋገጥ ብዙ ስራዎች እንደሚቀሩ ያስረዳል።

በወር አበባ ንጽህና መጠበቂያዎች ላይ የቀረጥ ማሻሻያ ቢደረግም፣ አቅርቦቱን ለማሻሻል ብዙ ስራ ይጠይቃል
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:59 0:00

በኢትዮጵያ ተገቢውን የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ውይም በተለምዶ አጠራሩ ሞዴስ በማጣት ምክንያት ትምህርታቸውን ያቋረጡ፣ በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘት ባለመቻላቸውም ለትዳር ወይም ለስደት የታደረጉ ሴት ተማሪዎች በርካታ ናቸው።

በዋጋ መናር ምክንያትም 72 በመቶ የሚሆኑት በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖሩ ወጣት ሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ሞዴሶችን እንዳማያገኙ የኢትዮጵያ የስነ-ህዝብ፣ ጤናና አካባቢ ጥበቃ ጥምረት የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ያጠናው ጥናት ያሳያል።

የዚህ ዋጋ ንረት ዋና ምክንያቱ ደግሞ በምርቱ ላይ ተጭኖ የነበረው ከፍተኛ ቀረጥ መሆኑን ጀግኒት የተሰኘው የሰላም ንቅናቄ ጥምረት መስራች የሆነችው ማራኪ ተስፋዬ ትገልፃለች።

በዚህ ከፍተኛ ዋጋ ምክንያት በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል ብቻ ሳይሆን፣ በከተሞችም የሚኖሩ በርካታ ሴት ተማሪዎች የወር አበባቸው በሚመጣበት ወቅት በሚጠቀሟቸው ተገቢ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ለተለያዩ የማህፀን በሽታዎች እንደሚጋለጡም ጭምር ማራኪ ታስረዳለች።

በወር አበባ ምክንያት በርካታ የኢትዮጵያ ሴት ተማሪዎች ሊያገኙት የሚገባቸውን ትምህርት እንደሚያጡ የነገሩን ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴር የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ወይዘሮ የሻረግ ነጋሽ ናቸው።

የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ካለማግኘት ጋር ተያይዘው በሴቶች ላይ በሚደርሱት በርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የስነ-ልቦና ቀሶች ምክንያት ጀግኒት ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት አመታት የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴርና የፕሬዝዳንቷን ፅህፈት ቤት ጨምሮ ከበርካታ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ጋር ሲሰራ ቆይቷል። በተለይ ግን ላለፉት ሶስት ወራት ማህበራዊ ሚኒያዎችን በመጠቀም የገንዘብ ሚኒስቴር በንፅህና መጠበቂያ ምርቶች ላይ ያለአግባብ ጥሎት የነበረውን ቀረጥ እንዲያነሳ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቶ በዚህ ሳምንት ውጤት ተገኝቷል።

በዚህም መሰረት የገንዘብ ሚኒስቴር የሴቶች የወር አበባ መጠበቂያና የህፃናት ንፅህና መጠበቂያ (ዳያፐር) በሀገር ወስጥ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ከውጭ የሚያስገቡት ጥሬ እቃ ከታክስ ነጻ እንዲሆን ያደረገ ሲሆን ከውጭ በሚገቡት ላይ ደግሞ ቀድሞ ቀድሞ የነበረው የታክስ ምጣኔ ወደ 10 በመቶ ዝቅ እንዲል አድርጓል፡፡

የቀረጥ ማሻሻያው ለመሰማታችን ማሳያ ነው የምትለው ማራኪ ማንኛዋም ሴት በወር አበባ ምክንያት ወደ ኃላ እንዳትቀር የሚደረገው ትግል ግን ገና ይቀጥላል ትላለች።

የቀረጥ ማሻሻያው አንድ ርምጃ ወደፊት የሚወስድ መሆኑን የገለፁት ወይዘሮ የሻረግም፣ የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ ወደፊት ቀረጥ ሙሉ ለሙሉ መነሳት እንደሚኖርበት አበክረው ይናገራሉ።

በአሁኑ ወቅት በኢትይጵያ 8 የሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ (ሞዴስ) አምራች ፋብሪካዎች እንዳሉ ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ጀግኒት ኢትዮጵያ እነዚህ ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ከመስራት ጎን ለጎንም በመፀዳጃ ቤት አቅርቦት ዙሪያ ላይም በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

XS
SM
MD
LG