በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የመገናኛ ብዙሃን የግጭት አዘጋገብ ሀላፊነት የጎደለው ነው - ምሁራን


ኢትዮጵያውያን ጋዜጣ እያነበቡ። (ፎቶ ሙሉጌታ አየነ)
ኢትዮጵያውያን ጋዜጣ እያነበቡ። (ፎቶ ሙሉጌታ አየነ)

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች የሚነሱ ግጭቶችና የሚፈጠሩ አለመረጋጋቶች በተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጪ መገናኛ ብዙሃን ይዘገባሉ። ሆኖም በቅርቡ በትግራይ ክልል የተካሄደውን ግጭት ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ አለመረጋጋቶችን መገናኛ ብዙሃን የሚዘገቡበት መንገድ በአብዛኛው ሀላፊነት የጎደለው ነው ሲሉ ምሁናን አስተናየታቸውን ይሰጣሉ። ለመሆኑ በግጭት ዘገባ ወቅት የመገናኛ ብዙሃን አዘጋገብ ምን መምለል አለበት? ሀላፊነታቸውስ እስከ ምን ድረስ ነው?

የመገናኛ ብዙሃን የግጭት አዘጋገብ ሀላፊነት የጎደለው ነው - ምሁራን
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:35 0:00


ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ለተደጋጋሚ ግጭቶች፣ የሰው ህይወት መጥፋት፣ መፈናቀል እና የንብረት ውድመት እየዳረገ ነው። እነዚህ ግጭቶችና ጥለውት የሚሄዱት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የስነ-ልቦና ቀውሶችም በተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጪ መገናኛ ብዙሃን ይዘገባሉ። ሆኖም በግጭቶች ወቅት ከኢትዮጵያ የሚወጡ ዘገባዎች በአብዛኛው ሀላፊነት የጎደላቸውና ሁኔታውን የሚያባብሱ ናቸው ሲሉ የጋዜጠኝነት መምህራንና አጥኚዎች ይተቻሉ።

ከነዚህ አንዱ አቶ ሚኪያስ ሲሳይ በጋዜጠኝነት ያገለገሉ የኮምዩኒኬሽንና ሚዲያ ባለሙያ ናቸው። በኢትዮጵያና በኤርትራ መሃከል በነበረው ጦርነት ወቅትም የተባበሩት መንግስታት ካቋቋመው የሰላም አስከባሪ ጋር በመሆን መገናኛ ብዙሃንን የማስተባበር ስራ ሰርተዋል፣ የሰላም ጋዜጠኝነት ላይም ጥናት አጥንተዋል። ታዲያ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩት የግጭት አዘጋገቦች እውነትን የማጣራትና የሚዛናዊነት ችግር በስፋት ይታይባቸዋል ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

መገናኛ ብዙሃን የህዝብ አይንና ጆሮ ናቸው የሚሉት አቶ ሚኪያስ በአሁኑ ወቅት ጫፍ ይዘው የሚዘግቡ ጋዜጠኞች መብዛት በህብረተሰቡ ላይ የሚያደርሰው ተፅእኖ የከፋ መሆኑንም እንዲህ ያስረዳሉ።

ጋዜጠኝነት በማንኛውም ወቅት ቢሆን እውነት ላይ መሰረት ያደረገ ሚዛናዊ መረጃዎችን ማቅረብ የሚጠይቅ ሙያ ነው። ይህ ሀላፊነት በተለይ በግጭት ወቅት የከበደ እንደሚሆንና የተለየ ጥንቃቄ እንደሚፈልግ የሚገልፁት ደግሞ በሚሲሲፒ ዩንቨርስቲ የጋዜጠኝነት ክፍል መምህር የሆኑት ዶክተር ዘነበ በየነ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ የሚወጡ ዘገባዎች ጉዳዮችን የሚያራግቡና ስሜታዊነት የሚታይባቸው ናቸው የሚሉት ዶክተር ዘነበ እውነታዎችም ቢሆኑ እንኳን እንደወረዱ ማቅረብ ተገቢ እንዳልሆነ ይገልፃሉ።

መገናኛ ብዙሃን ሀላፊነታቸውን ሲወጡ ሀገርን ከአደጋ ማዳን ይችላሉ የሚሉት ዶክተር ዘነበ በጎረቤት ሀገር ሩዋንዳና የቀድሞ ዩጎዝላቪያ አካል በነበረችው ኮሶቮ በአልባኒያና በሰርቢያን ብሄሮች መሃል በደረሰው እልቂት የመገናኛ ብዙሃን ሀላፊነት የጎደለው ዘገባ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደነበረው ያስታውሳሉ።

ባለፉት አመታት በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን እንቅስቃሴ ዙሪያ የተለያዩ መሻሻሎች ቢታዩም በአሁኑ ወቅት የሚታየው የግጭት አዘጋገብ ግን ሙያው አሁንም ብዙ ስልጠናዎችንና ጥናቶችን እንደሚጠይቅ ያሳየ መሆኑን ባለሙያዎቹ ያሰምሩበታል። በተለይ ማህበራዊ ሚዲያ የተቋም ሚዲያዎች ላይ ሀይሉን ያሳየበት ጊዜ ነው የሚሉት ዶክተር ዘነበ በቅርብ ግዜ በማህበራዊ ሚዲያ በተሰራጨ ፕሮፓጋንዳ ምክንያት በማይማር በሚገኙ ሙስሊሞች ላይ የደረሰው እልቂት በኢትዮጵያም እንዳይደገም ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አበክረው ይገልፃሉ።

በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ፅንፍ የያዙ መረጃዎች በህብረተሰብ መሀከል ያለውን ክፍፍል እያሰፋ መሆኑን አቶ ሚኪያስም ይስማሙበታል። አንዴ የተሰራጨን ሀሰተኛ መረጃ ማረም አስቸጋሪና ጊዜ የሚወስድ ነው የሚሉት አቶ ሚኪያስ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት በማህበራዊ ሚዲያ የሚወጡ መረጃዎችን እየተከታተሉ የሚያርሙበት አሰራር እንዲኖራቸው ይመክራል።

እ.አ.አ. በ 2008 በኬንያ የተደረገውን ምርጫ ተከትሎ በተነሳውን የብሄር ግጭት የከፋ ጉዳት ሳያደርስ እንዲቆም የመገናኛ ብዙሃን ትልቅ ሚና እንደተጫወቱ ባለሙያዎቹ ያስታውሳሉ። በኢትዮጵያም የመገናኛ ብዙሃን በተለይ ለግጭት ወቅት የተለየ የአዘጋገብ ደንብ በማዘጋጀት፣ ከግለሰባዊ ስሜት የፀዳና፣ ማጣራት የተደረገበት ሚዛናዊ ዘገባዎችን በማውጣት ሀገር ላይ የሚደርሱ አሉታዊ ተፅእኖዎችን በመቀነስ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ይመክራሉ።

XS
SM
MD
LG