ተሰናባቹን 2020 ያክል የሰው ልጆችን የፈተነ አመት ኖሮ የሚያውቅ አይመስልም። በአውስትራሊያ ደኖች ውስጥ በተፈጠረ ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ የጀመረው አመት ከቻይና፣ ዉሃን ከተማ በተነሳ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እስካሁን ከ1.8 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ህይወት ቀጥፏል። ይህን ተከትሎም የአለም ኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ገብቷል፣ ተቋማት ተፈትነዋል።
በኢትዮጵያም ከነዚህ ዓለም አቀፍ ቀውሶች በተጨማሪ ውስጣዊ የፖለቲካ አለመረጋጋት የወለዷቸው ግጭቶች ለበርካቶች ህይወት መጥፋት፣ መሰደድና ንብረት መውደም ምክንያት ሆነዋል። ይህን መነሻ አድርገን በዚህ በምናገባድደው አመት ችግሮችን ለመፍታት የሀገር- ብሄር ግንባታ አስፈላጊነትና፣ የጋራ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚቻልባቸው ሀሳቦች ዙሪያ ሲሰሩ ከነበሩ ምሁራን መሀከል አንዱ የነበሩትን ዶክተር ዘነበ በየነን አመቱ እንዴት ተጠናቀቀ ስንል ጠይቀናቸዋል።
ኢትዮጵያውያን እንደ ህብረተሰብ ፈውስ የሚያስፈልጋቸው ግዜ ነው የሚሉት ዶክተር ዘነበ፣ መጪው 2021 ዓ.ም የበርካቶች ቁስል የሚሽርበት አመት እንደሚሆን ተስፋ ያደርጋሉ።
ሌላው በዚህ 2020 ዓ.ም. ለኢትዮጵያኖች ከባድ የነበረው የኢኮኖሚ ቀውስና እያሻቀበ የሚሄደው የኑሮ ውድነት ነው። በዚህ ዙሪያ ከዚህ ቀደም የባለሙያ አስተያየታቸውን ሰጥተውን የነበሩት የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ ብስራት ተሾመ 2020 በአጠቃላይ በኢኮኖሚ አኳያ አስጨናቂ አመት እንደነበር ይገልፃሉ።
በኢኮኖሚው ዙሪያ ያለው ፈተና የበዛ ቢሆንም በዚሁ አመት በተለይ በቡና፣ በወርቅና በአበባ ንግድ ዙሪያ የታየው የውጪ ንግድ መሻሻል ተስፋ ሰጪ ነው። በመጪው አመትም ይህን መሻሻል አጠናቅሮ መቀጠል እንደሚገባ የሚገልፁት አቶ ብስራት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚታዩት ግጭቶችና የታቀደው ምርጫ ሊያደርሱ የሚችሉትን ተጨማሪ አሉታዊ ተፅእኖዎች ለመቀነስ መንግስት በተለይ ሰላምና መረጋጋት ላይ ጠንክሮ መስራት አለበት ሲሉ ይመክራሉ።
በምናገባድደው አመት በኢትዮጵያ በየጊዜው ከሚነሱት ግጭቶች ጎን ለጎን ተያይዞ በስፋት የተነሳው የሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭት ነው። በአሜሪካን አገር የሚገኘው ሀምሊን ዩንቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑትና በተለይ በኢንተርኔትና ሚህበራዊ ሚድያዎች ዙሪያ ሰፊ ጥናቶችን ያካሄዱት እንዳልካቸው ጫላ 2020 እውነትን ከሀሰት መለየት ከባድ የነበረበት አመት እንደሆነ ይገልፃሉ።
በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች ህብረተሰቡ ለበርካታ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ጉዳቶች እንደተጋለጡ አበክረው የሚገልፁት እንዳልካቸው በተለይ በመጪው የፈረንጆቹ አመት በሚካሄድው ምርጫ ተጨማሪ ጉዳቶች እንዳይደርሱ ሊሰሩ ስለሚገባቸው ስራዎች እንዲህ ያስረዳሉ።
2020 በተለይ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን፣ የጥላቻ ንግግሮችንና ጥቃት ቀስቃሽ መልዕክቶችን ለማስቆም የማህበራዊ ድህረ-ገፅ ተጠቃሚዎች እንቅስቃሴ የጀመሩበት አመትም ነበር። ከነዚህ አንዱ ደግሞ ዩሀንስ ሞላ ነው።
በአጠቃቀም ጉድለት ምክንያት ቴክኖሎጂ በማህበረሰብና በሀገር ላይ ጉዳት እንዲያደርስ ምክንያት ሆኖ ቢነሳም፣ በተለይ ባለንበት ወረርሽኝ ወቅት ቴክኖሎጂ የብዙ ሰዎችን ህይወት ያቀለለና ለብዙ ኢትዮጵያውያን ስራ የፈጠረ እንደሆነ የሶፍትዌር ኢንጅነርና በሎስ አንጀለስ ውስጥ የሚገኘው ሲቲ ናሽናል ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆነው ዮሴፍ አዱኛ ይገልፃል። ያዮቢ ሲል ባቋቋመው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት ቤት በዚህ አመት ብቻ ከ200 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያኖችን በነፃ ያሰለጠነው ዮሴፍ፣ ቴክኖሎጂን ለመልካም ስራ ካዋልነው በቀጣይ አመታት ህይወታችንን የሚቀይር ነው ይላል።
እነዚህን አውንታዊና አሉታዊ ሁነቶችን ያስተናገደው 2020ን ተሰናብተናል። ብዙዎችም ያለፉትን ፈተናዎች ረስተው አዲሱን 2021 በብዙ ተስፋ ሊቀበሉት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል። እኛም የፈረንጁን አዲስ አመት ለሚያከብሩ መልካም አዲስ አመት እንዲሆን እንመኛለን።