በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“ጉግል ነገረኛ ጥቁር ሴት አስመስሎኛል” - ትምኒት ገብሩ


በሰው ሰራሽ ልህቀት ዙሪያ ስላሉ መድልዎችና ፍትሃዊነት በርካታ ጥናት ያደረገቸውና፣ በድንገት ከስራዋ በመባረርሯ በአለም ዙሪያ ትልቅ መነጋገሪያ የሆነችው ትምኒት ገብሩ
በሰው ሰራሽ ልህቀት ዙሪያ ስላሉ መድልዎችና ፍትሃዊነት በርካታ ጥናት ያደረገቸውና፣ በድንገት ከስራዋ በመባረርሯ በአለም ዙሪያ ትልቅ መነጋገሪያ የሆነችው ትምኒት ገብሩ

ከጉግል ካምፓኒ ከሳምንታት በፊት በድንገት የተሰናበተችው የሰው ሰራሽ ልህቀት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ባለሙያ ትምኒት ገብሩ የቀድሞ የስራ ባልደረቦች፣ ትምኒት እድገት ተሰጥቷት ወደ ስራዋ እንድትመለስ በደብዳቤ ጠይቀዋል። ትምኒት ግን ከጉግል ጋር ያለኝ ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ አብቅቷል ስትል ለአሜሪካ ድምፅ ተናግራለች። ጉግል ትምኒት ከስራ የተሰናበተችበት መንገድ ለፈጠረው ጥርጣሬ ይቅርታ ቢጠይቅም፣ ትምኒት ይቅርታው ለኔ አልቀረበም ስትል አልተቀበለችውም።

ጉግል ነገረኛ ጥቁር ሴት አስመስሎኛል - ትምኒት ገብሩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:34 0:00

የሰው ሰራሽ ልህቀት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ተመራማሪዋ ትምኒት ገብሩ ትውልድና እድገቷ በአዲስ አበባ ነው። ናዝሬት የሴቶች ትምህርት ቤትም ተምራለች። የኤሌክትሪካል ምህንድስና ባለሙያ ከሆኑት ቤተሰቦቿ ጋር ወደ አሜሪካ ከመጣች በኃላ የአባቷንና የእህቶቿን ፈለግ በመከተል በስታንፎርድ ዩንቨርስቲ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪዋን በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተመርቃ ከአፕል ጋር ሰርታለች። የዶክትሬት ዲግሪዋን ለመማር ተመልሳ ወደ ስታንፎርድ በገባችበት ወቅት ግን የሰው ሰራሽ ልህቀት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ጉዳይ የበለጠ እየሳባት መጣ። ምክንያቱ ደግሞ በሙያው የጥቁሮች ተሳትፎ እጅግ አናሳ መሆኑና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ኢ-ፍትሃዊ መሆን እንደነበር ትምኒት ትናገራለች።

ትምኒት የቴክኖሎጂ ውጤቶች አካታች እና ፍትሀዊ እንዳልሆኑ ማሳየት የጀመረችው ስታንፎርድ እያለች የሰዎችን የፊት ገፅታ በማየት ማንነታቸውን የሚያውቅ (ፌሽያል ሪኮግኒሽን) የተባለው መተግበሪያ ላይ በሰራችው ጥናት ነው።

ትምኒት ጥቁሮችም ሆኑ ሴቶች በብዛት በማይገኙበት እንደ ማይክሮሶፍት የመሳሰሉ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ውስጥ ፍትሀዊነት፣ ግልፅነት እና ሥነ-ምግባር ላይ ከሚሰሩ ቡድኖች ጋር ሰርታለች፣ ብዙ ጥናቶችንም አካሂዳለች። የዛሬ ሁለት አመት ጉግልን ከተቀላቀለች በኃላም የሰው ሰራሽ ልህቀት ሥነ-ምግባር ዘርፍ ባልደረባ ሆና የቴክኖሎጂ ውጤቶች አካታች ሊሆኑ በሚችሉባቸው መንግዶች ዙሪያ ጥናት ስታካሂድ ቆይታለች። አሁን ከስራ ለመሰናበቷ ምክንያት የሆነውና በቅርቡ ስራ ላይ በዋለ የቋንቋ ቴክኖሎጂ ዙሪያ ያካሄደችው ጥናት ታዲያ ጉግልን ለምን አስቆጣው ስንል ትምኒትን ጠይቀናታል።

ጉግል ትምኒት ያካሄደችው ጥናት በሙያው ውስጥ ባሉ ሰዎች ተገምግሞ አስፈላጊውን መስፈርት አላሟላም በማለት ጥናቱ ይቀርብበት በነበረው ኮንፈረንስ ላይ እንዳታካትት ወይም ከጥናቱ ውስጥ ስሟን እንድታወጣ ጠይቋታል። ያንን ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆኗ እራሷ ባቀረበችው የመልቀቂያ ጥያቄ መሰረት እንዳሰናበታትም ገልጿል። ትምኒት ግን እኔ መልቀቂያ አላቀረብኩም፣ በጉግል የተነገሩት ምክንያቶችም እውነት አይደሉም ትላለች።

ጉግልን ጨምሮ በርካታ የቴክኖሎጂ ካምፓኒዎች ብዝሃነት እና አካታችነት በድርጅታቸው ፖሊሲ ውስጥ በግልፅ ተቀምጧል። ለፆታና የዘር እኩልነት እንደሚሰሩም በተለያዩ አጋጣሚዎች ይናገራሉ። ይሄ ፖሊሲ ከወሬ የዘለለ አይደለም የምትለው ትምኒት ግን በተቃራኒው በቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ዘረኝነት በሰፊው እንደሚታይ አጥብቃ ትናገራለች።

ትምኒት ከጉግል መባረሯ በመገናኛ ብዙሃንና በቴክኖሎጂ ዘርፉ ውስጥ ባሉ በርካታ ሰዎች ዘንድ መነጋገሪያ መሆኑን ተከትሎ የካምፓኒው ዋና ስራ አስኪያጅ ሳንደር ፒቻይ በሰራተኞች ዘንድ ለፈጠርው የእምነት ማጣት ይቅርታ ጠይቀዋል። ትምኒት ግን ይቅርታው ለሷ እንዳልተላለፈ በመግለፅ፣ በምትኩ እኔን ነገረኛ ጥቁር ሴት አስመስለውኛል ትላለች።

ትምኒት የቴክኖሎጂ ዘርፉ ኢፍትሃዊ መሆን ጥቁሮችንም ሆነ ሴቶችን ወደ ዘርፉ እንዳይመጡ ሊያግዳቸው አይገባም ትላለች። እንደውም በሙያው ጠንክረው በመስራት ማሸነፍ እንደሚችሉ ሊያሳይ ይገባል ስትልም ትመክራለች።

ትምኒት ከዚህ በኃላ ከጉግል ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደማይኖራትና በአሁኑ ሰዓት ከሷ ጋር በተመሳሳይ ሙያ ውስጥ ከምትገኘው ረድኤት አበበ ጋር በመሆን ባቋቋመችው ብላክ ኢን ኤ አይ የተሰኘ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ላይ አተኩራ እየሰራች እንደሆነ አስረድታናለች። ቀጣይ የሙያ ጉዞዋንም ገና እያሰበችበት እንደሆነና እስካሁንም ምንም አይነት የቅጥር ጥያቄ እንዳልተቀበለችም ገልፃለች።

XS
SM
MD
LG