በግዙፉ የአሜሪካ የመድሃኒት አምራች ኩባንያ ፋይዘር እና የጀርመኑ የሕክምና ቴክኖሎጂ ኩባንያ ባዮንቴክ በጋራ የሰሩት የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት በአሜሪካን አገር መሰጠት ከጀመረ አንድ ሳምንት አስቆጠረ።
ኒዮርክ ፍለ ግዛት ሎንግ አይስላንድ ጅዊሽ በተሰኘ የጤና ተቋም ውስጥ የምትሰራዋ ነርስ ሳንድራ ሊንድሴይ የመጀመሪያውን ከቤተ ሙከራ ውጪ የተሰጠውን ክትባት ከወሰደች በኋላም በርካታ የጤና ባለሞያዎችና ሌሎች ለቫይረሱ ተጋላጭ ሆነው የሚሰሩ ባለሙያዎች በቅድሚያ ክትባቱን እየወሰዱ ይገኛሉ።
ለመሆኑ የኮቪድ 19 ክትባት አወሳሰድ ምን አይነት ነው? ክትባቱ ከተወሰደ በኃላ የሚኖረው ስሜትስ ምን ይመስላል? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ባለፈው ሳምንት ክትባቱን ከወሰዱ የመጀመሪያ የጤና ባለሙያዎች መሃል አንዱ የሆነውንና ኮሎራዶ ክፍለ ግዛት ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ቻፕሊን ሆኖ በሽተኞችን የማማከር አገልግሎት የሚሰጠውን ኢታና ጨመዳ ዲሳሳን ጋብዘናል።