በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጆዜፍ ሮቢኔት ባይደን 46ኛው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የሚያደርጋቸውን የዘንድሮ ምርጫ ማሸነፋቸው ተነገረ


የኦባማ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆዜፍ ሮቢኔት ባይደን 46ኛው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የሚያደርጋቸውን የዘንድሮ ምርጫ ማሸነፋቸው ተነገረ።

ወደ ግማሽ ምዕት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ዋሺንግተን ፖለቲካ ውስጥ የቆዩት ጆ ባይደን በዕድሜ እጅግ የገፉ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ።

ከጆ ባይደን ጋር የተወዳደሩት ካማላ ሃሪስ የመጀመሪያዋ ሴት እና ጥቁር ምክትል ፕሬዚዳንት እንደሚሆኑም ታውቋል።

የዜና ተቋማት ባይደን የምርጫው አሸናፊ መሆናቸውን ያሳወቁት እጅግ በተካረረ የምርጫ ዘመቻና አሁንም ገና ጨርሶ ባልተጠናቀቀው ንትርክ የበዛበት የድምፅ ቆጠራ ላለፉት አራት ዓመታት ሃገሪቱን የመሩትን ዶናልድ ትረምፕን አሸንፈው ነው።

ጆ ባይደን ምርጫውን ማሸነፋቸው የተነገረው የብርቱ ትንቅንቅ ሜዳ ከሆኑት ግዛቶች አንዷ የሆነችውን ሃያ የባለድምፅ ልዑካን ያሏትን የእርሳቸውም የትውልድ ቦት የሆነችውን ፔንሲልቬንያን መርታታቸው ከተገለፀ በኋላ ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ለመሆን በሙሉ ግዛቶቹ ካሉት 538 ባለድምፅ ልዑካን የ270ውን ማግኘት የሚያስፈልግ ሲሆን የባይደን የፔንሲልቬንያ ድል ያጎናፀፏቸው ሃያ ድምፆች ያንን የማሸነፍ ጣሪያ አስልፎ 273 አድርሷቸዋል።

ውጤታቸው ገና ያልተረጋገጠ ሌሎች አራት ግዛቶች ድምፆች ቆጠራ አሁንም እንደቀጠለ ነው።

ምርጫው በስፋት ተጭበርብሯል የሚሉት የፕሬዚዳንት ትረምፕ ዘመቻ በብዙ ግዛቶች ውስጥ ክሦችን መሥርቷል፤ ሌሎች ዶሴዎችን ለመክፈትም ሲዘጋጅ መቆየቱ ተዘግቧል።

XS
SM
MD
LG