በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕና ባለቤታቸው ሜላንያ የተላለፈ የመልካም ምኞት መልዕክት


የፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕና ባለቤታቸው ሜላንያ ትራምፕ
የፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕና ባለቤታቸው ሜላንያ ትራምፕ

የአሜሪካ ምርጫ ሊደረግ ወደ አንድ ወር ገደማ በቀረበት ጊዜ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ለተረጋገጠው የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕና ባለቤታቸው ሜላኒያ ትራምፕ ከተለያዩ የዓለም ባለሥልጣናት የእግዚያብሔር ይማራችሁ መልዕክት እየተላለፈላቸው ነው።

please wait

No media source currently available

0:00 0:05:45 0:00

የፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕና ባለቤታቸው ሜላንያ ትራምፕ በኮሮና ቫይረስ መያዝ ዜና ተከትሎ በአለም ዙሪያ የሚገኙ መሪዎችና ታዋቂ ገለሰቦች የመልካም ምኞት መገለጫዎች እያስተላለፉ ነው። ምክትል ፕሬዚደንታቸው ማይክ ፔንስ በትዊተር ባወጡት የመልካም ምኞት መግለጫ " ከኬረን ጋር ሆነን ለውዶቹ ጉዋደኞቻችን ለፕሬዚደንት ትረምፕ እና ለቀዳማዊት ዕመቤት ሚላንያ ፍቅራችንን እንገልጻለን፥ እንጸልያላቸዋለን ፥ በመላዋ አሜሪካ ከሚሊዮኖች ጋር ሆነን በፍጥነት እንድታገግሙና ሙሉ ጤንነታችሁ እንዲመለስ እንጸልያለን፥ እግዚአብሄር ፕሬዚደንቱንና ቀዳማዊት ዕመቤትን ከነቤተሰባችሁ ይባርክ "ብለዋል።

የምክትል ፕሬዚደንቱ የፕሬስ ጸሃፊ ዴቪድ ኦማሊ በትዊተር ገጻቸው ባወጡት ቃልም ምክትል ፕሬዚደንቱና ባለቤታቸው ተመርምረው ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው መረጋገጡን ተናግረዋል። በክሮሽያ ጉዞ ላይ ያሉት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዎ በበኩላቸው ተመርመረው ኮቪድ እስራ ዘጠኝ እንዳልተያዙ አብረዋቸው ለተጉዋዙ ጋዜጠኞች ያረጋገጡ ሲሆን፣ እስከትለውም ፕሬዚደንቱና ባለቤታቸው ፈጥነው እንዲያገግሙ ጸሎቴ ነው ብለዋል።

በመጪው ምርጫ የዲሞክራቲክ ፓርቲው የፕሬዚደንቱ ተፎካካሪ የቀድሞው ምክትል ፕሬዚደንት ጆ ባይደንም በትዊተር ገጻቸው ለፕሬዝዳንቱና ለቀዳማዊት እመቤት ሚላንያ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል። "እኔና ጂል ፕሬዚደንት ትረምፕና ቀዳማዊት ዕመቤት ሚላንያ በቶሎ እንዲያገግሙ መልካም ምኞታችንን እንገልጻለን ፥ ለፕሬዚደንቱና ለቤተሰባቸው ጤናና ደህንነት እንጸልያለንም" ብለዋል ባይደን።

የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምም እንዲሁ ለፕሬዝዳንት ትራምፕ የመልካም ምኞት መገለጫቸውን በትዊተር ገፃቸው አማካኝነት አስተላልፈዋል። ዶክተር ቴድሮስ በመልክታቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ባለቤታቸው በፍጥነት ሙሉ ለሙሉ እንዲያገግሙ ተመኝተዋል።

ዶክተር ቴድሮስ የሚመሩት የአለም ጤና ድርጅት ኮቪድ 19 የአለም ወረርሽን መሆኑን ከመጋቢት ጀምሮ ያወጀ ሲሆን እስካሁንም ከ 34 ሚሊዮን ሰዎች በላይ በአለም ዙሪያ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከአንድ ሚሊየን በላይ ደግሞ ለህልፈት ተዳርገዋል። ከነዚህ ውስጥ 7.1 ሚሊዮን የሚሆኑት አብዛኛው የቫይረሱ ተያዦች በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ሲሆን ከ 205 ሺህ ሰዎች በላይ ለሞት መዳረጋቸውን የጤና ድርጅቱ መረጃ ያሳያል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ አርብ እለት ጠዋት በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን በትዊተር ገፃቸው ሲያሳውቁ በመጀመሪያ የመልካም ምኞት መግለጫቸውን ከላኩ የመጀመሪያ መሪዎች መሀል ቀዳሚው የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ናሬንድራ ሞዲ ናቸው። ሞዲ በትዊተር ገፃቸው እንዳሰፈሩት "ጉዋደኛዬ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ቀዳማዊት እመቤት ሜላንያ ትራምፕ ቶሎ እንዲያገግሙና በመልካ ጤንነት ላይ እንዲሆኑ እመኛለሁ" ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ በበኩላቸው ለፕሬዝዳንት ትራምፕና ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ቶሎ እንዲያገግሙ የመልካም ምኞት መግለጫቸውን አስተላልፈዋል።

በድህረ-ገፃቸው አማካኝነት መልክታቸውን ያስተላለፉት ሌላው የአለም መሪ ደግሞ የራሺያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ናቸው። ፑቲን ለፕሬዝዳንት ትራምፕ መልካም ጤና ተመኝተው "ጥንካሬህ፣ መልካም መንፈስህና ተስፈኝነትህ ከዚህ አደገኛ በሽታ ቶሎ እንድታገግም ይረዳሃል።" ብለዋል፣ በመልክታቸው።

ከ291 ሺህ በላይ የቫይረሱ ተጠቂዎች የሚገኙባት ጀርመን ቻንስለር አንጄላ ማርኬል በቃል አቀባያቸው አማካኝነት ባወጡት መግለጫም፣

"ለዶናልድ እና ሜላኒያ መልካም እመኝላቸዋለሁ። ከኮሮና ቫይረስ ቶሎ አገግመው ወደ ሙሉ ጤንነትታቸው እንደሚመለሱም ተስፋ አለኝ" ብለዋል።

መስከረም አጋማሽ ላይ ከባህሬንና ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጋር የሰላም ስምምነት ለመፈራረም ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ተገናኝተው የነበሩት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤንጃሚን ኔትናሁም እንዲሁ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በፍጥነት እንዲያገግሙ የሚገልፅ መልክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከአገር መሪዎች በተጨማሪ በቴክሳስ የዲሞክራቲክ ፓርቲን ወክለው የኮንግረስ አባል የሆኑት ጃኩዊን ካስትሮ በበኩላቸው ፕሬዝዳንቱ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው አሳሳቢ ነው ሲሉ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል። "ይሄ የፕሬዝዳንቱ የጤና ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሀገሩቱ ደህነት ጉዳይ ነው" ብለዋል ካስትሮ።

በአፍጋኒስታን የብሄራዊ መግባባት መማክርት ጉባኤ ሰብሳቢ የሆኑት አብዱላህ አብዱላህም የአሜሪካው ፕሬዝዳንትና ባለቤታቸው በፍጥነት እንዲሻላቸው በትዊተር ገፃቸው ላይ ያሰፈሩ ሲሆን "የአሜሪካ ህዝብ ይህን ወረርሽኝ በአሸናፊነት እንዲያልፉት እመኛለሁ" ሲሉ አክለዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕን በተደጋጋሚ በመንቀፍ የሚታወቁት የሲቪል መብት አቀንቃኙ ጄሲ ጃክሰን ጨምሮ ሌሎች ተቺዎቻቸውም በትዊተር መልክቶቻቸውን አስተላልፈዋል።

ጄሲ ጃክሰን በመልክታቸው፣ "ፕሬዝዳንቱና ቀዳማዊት እመቤት የዚህ በሽታ አስከፊ ገፅታ እንዳይደርስባቸውና በቶሎ እንዲያገግሙ እንፀልያለን። በየትኛውም ሀይማኖትም ሆነ የፖለቲካ አመለካከት ውስጥ ብንሆን፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በዚህ በሽታ ተጠቅተዋልና ሁላችንም ልንፀልይ ይገባል" ብለዋል።

XS
SM
MD
LG