ዋሽንግተን ዲሲ —
ዛሃራ ለገሰ የስነ ልቦና ባለሞያ እና የአስክ ዛሃራ የማሕበራዊ ሚዲያ ገጽ መስራች ናት፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በሚታተመው እና በነጻ በሚከፋፈለው የዋትስ አፕ መጽሄት ላይም አምደኛ ነበረች፡፡ ባለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት በሙያዋ ብዙዎችን አገልግላለች፡፡
ዛሃራ ከኮቪድ 19 ወርርሽኝ ወዲህ በወር አንዴ ወጣቶችን እየጋበዘች በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የምክር እና የውይይት አገልግሎት እየሰጠች ትገኛለች፡፡ በነዚህ ግዜያት ታዲያ ኪቪድ-19 በወጣቶች ስነ፟ልቦና ላይ ያደርሰውን ጫና ለመታዘብ ችላለች፡፡ ዛሃራ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የትምህርታቸው ጉዳይ እንደሚያስባቸው፣ ከቤተሰብ ጋር በአንድ ላይ ለረጅም ግዜ መቀመጥ ድብርት ስለፈጠረባቸው ረጅም ሰዓት በማሕበራዊ ደረገጾች ላይ እንድሚያጠፉ እና በማሕበራዊ ሚዲያው ላይ በእንግሊዘኛ ቡሊዪንግ የሚባለው በወጣቶች መሃከል ያለ መዘላለፍ እራስን እስከማጥፋት ደረጃ እያመራ መሆኑን ለጋቢና ቪኦኤ አጋርታለች፡፡
ለወጣቶቹ በጓደኞቻቸው ዘንድ ቦታ ማግኘት ትልቅ ጉዳይ እንደሆነባቸው የምትገልጸው ዛሃራ ወጣቶች እራሳቸውን እንዲሆኑ ከጓደኛ እና ከሱስ፣ ተጽእኖ እንዴት መላቀቅ እንደሚችሉም አጋርታለች፡፡