ዋሽንግተን ዲሲ —
የዮናይትድስ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ጄ ትራምፕ የዘንድሮውን የሂሳብ እና ሳይንስ ትምህርት እንዲሁም የሳይንስ ፣ ሂሳብ እና ምህንድስና ስልጠና ዘርፎች ለሚሰጠው የላቀ ፕሬዚደንታዊ ሽልማት የተመረጡ ግለሰቦችን በመስሪያ ቤታቸው በኩል ይፋ አድርገዋል።በሀገሪቱ ከሚገኙ 50 ግዛቶች ከተመረጡት አሸናፊዎች መካከል አንዱ በሳቫና ስቴትስ ዩኒቨርሲቲ የሂሳብ ትምህርት ክፍል ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ሙላቱ ለማ መሆናቸው ተበስሯል።
ዶ/ር ሙላቱ ከ25 ዓመታት በላይ በከፍተኛ ትምህርት አስተማሪነት የቆዩ እና ከ100 በላይ የምርምር ጽሁፎችን ያበረከቱ ሊቅ ናቸው።በሳይንስ ፣ ሂሳብ እና ምህንድስና ስልጠና ዘርፍ ካሸነፉ 12 ሰዎች መካከል አንደኛው ሆነው በመመረጣቸው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ፊርማ ያረፈበት የክብር ምስክር ወረቀት እና ከብሄራዊ ሳይንስ ፋውንዴሽን የተበረከተ የገንዘብ ጉርሻ ያገኛሉ።
"ሽልማቱ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሽልማትም ነው!" ሲሉ ለአሜሪካ ድምጽ የተናገሩት ዶ/ር ሙላቱ ፣ዕውቀታቸውን ለወጣት ኢትዮጵያዊያን ለማሸጋገር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸውም ተናግረዋል።
ሙሉ ዘገባውን ያዳምጡ።