በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ተደጋጋሚ የፖለቲካ አለመረጋጋትና ግጭቶች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ እያስከተሉ ነው


ፎቶ ፋይል
ፎቶ ፋይል

ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋትና፣ የሰላም እጦት፣ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ እያደረሰ ካለው ቀላል የማይባል ጥፋት ባለፈ በህብረተሰቡ ውሰጥ ጥሎት የሚያልፈው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የስነ-ልቦና ቀውስ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው የኢኮኖሚና ማህበራዊ ኑሮ ተንታኞች ገልጸዋል።

የዋጋ ንረት፣ ስራ አጥነት፣ የሀገር ውስጥና የውጪ ባለሀብቶች መመናመን፣ የአቅርቦት እጥረትና የውጪ ንግድ ምርቶች ገዢዎች መቀዛቀዝ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ በሚከሰቱ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች ምክንያት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ እየደረሱ ያሉ ተፅእኖዎች ናቸው። ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየተበራከቱ በሄዱት ሁከቶች ውስጥ የሚስተዋሉት መንገዶች የመዝጋት፣ ንብረት በማውደም የስራ አጥነት እንዲባባስ ማድረግና ሀገራዊ ዋጋ ያላቸውን እሴቶችን ማጥፋት በተለይ ቀጥተኛ ባልሆነው የኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ ተመርኩዞ የሚኖረውን አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ገቢ እያሳጣ መሆኑን የኢኮኖሚ ተንታኝ የሆኑት አቶ ዋሲሁን በላይ ያስረዳሉ።

የሀገር አለመረጋጋት በኢኮኖሚው ላይ ከሚፈጥራቸው ሌሎች ውስብስብ ችግሮች መሀል የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ በሆኑት የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ላይ የሚደረሰው ስጋት፣ ፍርሀትና ጥቃት ነው።

ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረው ሁከት ብቻ 195 ሆቴሎችና 6 የማምረቻ ፋብሪካዎች መቃጠላቸውን፣ 32 ሆቴሎች ላይ የመሰባበር ጉዳት መድረሱንና 104 የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ላይ የቃጠሎ ውድመት መድረሱን የክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ባልቻ ትላንት ለአሜሪካ ድምፅ አስታውቀው ነበር። አቶ ዋሲሁን ይሄ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ ጉዳት ነው ይላሉ።

በኢትዮጵያ የሚታዩት ግጭቶች መባባስ በኢኮኖሚው ላይ ከሚያሳድረው አሉታዊ ተፅእኖ ጎን ለጎን በህብረተሰቡ ውስጥ ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ቀውስ እንደሚያስከትል የሚገልፁት ደግሞ በሚሲሲፒ ዩንቨርስቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪ ዶክተር ዘነበ በየነ ናቸው።

ከአመታት በፊት በሩዋንዳ የተካሄደውን የዘር ጭፍጨፋ በቅርበት ያጠኑት ዶክተር ዘነበ፣ ዘርን መሰረት ባደረገ ፖለቲካ ውስጥ የመበደልና የመገፋት ስሜትን በመፍጠር 'እኛና እነሱ' የሚል መከፋፈል ሊያመጣ የሚችል መሆኑን በመግለፅ፣ ይህ አይነቱ መከፋፈል ወደማይታረቅ ልዩነት ይመራል ሲሉ ስጋታቸውን ያጋራሉ።

ከላይ የተነሱትን ፓለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታትም ሆነ ህብረተሰቡን ከተደጋጋሚ ጥቃቶች የመጠበቅ ዋናው ሀላፊነት የመንግስት መሆኑን የሚስማሙት ያነጋገርናቸው ምሁራን፣ መሰረታዊ ችግሮችን ስር ነቀል በሆነ መልኩ መፍትሄ በመፈለግ፣ ለሰዎች ደህነት ዋስትና በመስጠትና ፓለቲካውን በማረጋጋት ኢኮኖሚውን መደገፍ፣ ህብረተሰቡንም ከገባባት ቀውስ ማዳን ይቻላል ሲሉ ይመክራሉ።

ተደጋጋሚ የፖለቲካ አለመረጋጋትና ግጭቶች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ እያስከተሉ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:08 0:00


XS
SM
MD
LG