የድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ በኢትዮጵያ ለሁለት ሳምንት ሙሉ ለሙሉ የተቋረጠው የኢንተርኔት አገርልግሎት ሀገሪቱን በቀን ከ 4 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደሚያሳጣት በዓለም ላይ የኢንተርኔት ስርጭትንና የሳይበር ደህንነትን የሚከታተለው 'ኔት ብሎክስ' የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አስታውቋል። የኢትዮጵያ መንግስት አገልግሎቱን ያቋረጠው ከድምፃዊው ሞት በኃላ የተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ እንዳይባባስ፣ ብሎም የሰዎችን ሕይወትና ንብረት ከጥቃት ለመጠበቅ መሆኑን ቢገልፅም፣ መንግስትን ጨምሮ በኢንተርኔት ግንኙነት ላይ ጥገኛ ሆነው የሚሰሩ የንግድ ተቋማት ለከፍተኛ ክስረት መዳረጋቸውን ያነጋገርናቸው የሀገር ውስጥ የንግድ ተቋማትና የኢኮኖሚ ተንታኞች አስረድተዋል።
የድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በኢትዮጵያ ለሁለት ሳምንት ሙሉ ለሙሉ ተዘግቶ የቆየው የኢንተርኔት አገልግሎት ለሀገሪቱ በዋናነት የኢንተርኔት አቅራቢ የሆነውን ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ፣ የባንክና ፋይናንስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትንና የንግድ ድርጅቶችን ለከፍተኛ ክስረት ዳርጓል። የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው በዋናነት ኢንተርኔትን መሰረት አርገው አገልግሎት የሚሰጡት ዛይ ራይድና ዴሊቨር አዲስ የተሰኙት ሁለት የንግድ ተቋማት ባሳለፍነው ሁለት ሳምንት ውስጥ ብቻ በአማካይ ከ 50 ሺ እስከ 200 ሺህ ብር የሚሆን የቀን ገቢ ማጣቸውን ገልፀዋል።
የአዲስ አበባን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ የዛሬ አምስት አመት ስራ የጀመረው ዛይ ራይድ የዘመናዊ ታክሲ አገልሎት የኢንተርኔት በተቋረጠባቸው አስር ቀናት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ስራ እንዲያቋርጥ በመገደዱ ድርጅቱ ሊያገኘው አቅዶ የነበረውን ከ 500 ሺህ ብር የሚበልጥ ገንዘብ ማጣቱን የድርጅቱ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ሀብታሙ ታደሰ ይናገራሉ።
በስሩ ከ 40 በላይ ተቀጣሪዎችንና ከ700 በላይ አሽከረካሪዎችን የሚያስተዳድረው ዛይ ራይድ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ቀድሞውንም ገበያ ቀዝቅዞበት እንደነበር የሚያስረዱት አቶ ሀብታሙ ለሀገር ደህንነት ብሎ መንግስት የወሰደውን ኢንተርኔት የመዝጋት ውሳኔ ቢደግፉም፣ አዘጋጉ የንግድ ተቋማትን በማይጎዳ መልኩ መሆን ይችል ነበር ይላሉ።
በተመሳሳይ በአዲስ አበባ የምግብ፣ ግሮሰሪ፣ አበባና ሌሎች የፍጆታ ምርቶች አቅራቢ የሆነው፣ የዴሊቨር አዲስ ድርጅት መስራች ፈለግ ፀጋዬ፣ ድርጅታቸው ኢንተርኔት በተቋረጠባቸው እያንዳንዱ ቀኖች ከ 200 ሺህ ብር በላይ ማጣቱን ተናግረዋል።
የኢንተርኔት መዘጋት በሀገሪቱ ውስጥ የገዘፈ ችግር መኖሩን ማሳያ ነው የሚሉት አቶ ፈለግ፣ ማንኛውም ሰው በሀገሩ ላይ ሰርቶ ለመኖር በቅድሚያ ደህንነት እና ጥበቃ ሊኖረው ይገባል ይላሉ።
ከግል የንግድ ተቋማት ባሻገር ባንኮች፣ የመረጃ ቴክኖሎጂ ተቋማትና የጉዞ ወኪሎች በኢንተርኔት መቋረጥ ተጠቂ ከሆኑት መሀል ናቸው። በተለይ ባንኮች የሚሰጧቸው ከወጪ ንግድ ጋር የተያያዙ ስራዎችና የሐዋላ ገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎች ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንደሚያሳድር የገለፁልን በንስር ማይክሮፋይናንስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ዳዊት ፀጋዬ ናችው።
ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ በሚከተሰው የኢንተርኔት መዘጋት ምክንያት የሚፈጠረው የግንኙነት መቋረጥ ሀገሪቷን በቀን እስከ 4 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ትልቅ ገቢ እንደሚያሳጣትም አቶ ዳዊት አስረድተዋል።
በጉዳዩ ላይ ያናገርናችው የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኝ አቶ ዋሲሁን በላይ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነፃፀር የኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ በጣም ዝቅተኛ የሚባል ቢሆንም በሀገሪቱ ውስጥ በቀጥታ ከኢንተርኔት ጋር ግንኙነት ያላቸው ስራ የሚሰሩ
በርካታ ተቋማት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ገቢያቸውን ማጣታቸውን ገልፀው በዋናነት ተጎጂ የሆነው ግን መንግስት ራሱ ነው ይላሉ።
አቶ ዋሲሁን፣ መንግስት በሀገር ደህንነት ላይ የተጋጠን አደጋ ከመከላከል በሚል ያቋረጠው የኢንተርኔት አገልግሎት በሀግሪቱ ላይ ያደረሰው የኢኮኖሚ ተፅእኖ ቀላል ባይሆንም፣ የሀገርን ህልውና ከማስጠበቅ አንፃር ግን አትራፊ ነበር ይላሉ።
የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በሆነችው ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ የኢንተርኔት መቋረጥ ሲከሰት ከሀገር ኢኮኖሚ ባሻገር ዓለም አቀፍ ግንኙተቶችንም እንደሚጎዳ የሚያስረዱት የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ ዋስይሁን፣ የኢንተርኔት መቋረጥ ግድ በሚሆንበት ግዜ ኢምባሲዎች፣ ዲፕሎማቶችና ሌሎች መሰረታዊ የኢኮኖሚ ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ አካላትን በጅምላ የማያካትት ሊሆን እንደማይገባ አሳስበዋል።