በየመንገዱ ዳር ወይም በየቆሻሻ መጣያውግ ውስጥ ወድቀው የሚታዩት ከፕላስቲክ የተሰሩ የእጅ ጕንቶች አሁንም በኮርኖና ቫይረስ ስጋት ውስጥ እንደምንኖር የእለት-ተእለት ማስታወሻችን ናቸው። በእንግሊዝ አገር የሚገኝ የፕላስቲክ ፕላኔት የተሰኘ ድርጅት የጋራ መስራች የሆኑት ሲያን ሱዘርላንድ፣ አገራት ዜጎቻቸውን ከዚህ ወረርሽኝ ለመጠበቅ በሚያደርጉት ትግል ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ፍላጎት እንዲጨምር ማድረጉን ያስረዳሉ።
"የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከጀመረ ወዲህ የፕላስቲክ ምርቶች መጠን ማሻቀብ ሁላችንም የምናስተውለው ነው። በተለይ ደግሞ በፕላስቲክ የተሰሩ የቫይረሱ መከላከያ ግብዓቶች ምርት እጅግ በጣም ጨምሯል።"
ሱዘርላንድ፣ የግብዓቶቹ ምርቶች ምን ያክል እንደጨመረ እንግሊዝን ምሳሌ አድርገው ሲያስረዱ፣ ወረርሽኙ አገሪቱ ውስጥ ከገባበት የካቲት መጨረሻ አንስቶ እስከ ሚያዚያ ባለው ጊዜ ወደ 750 ሚሊዮን የሚጠጋ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ግብዓት በእንግሊዝ አገር ለቫይረሱ የፊት ለፊት ተጋላጭ ለሆኑ ሰራተኞች እንዲከፋፈል ተደርጕል ይላሉ።
"ለአንድ ግዜ ተጠቅመን አውልቀን ወደ ቆሻሻ መጣያ የምንጨምራቸው ግብዓቶች ካልተቃጠሉ በስተቀር ለዘለዓለም ምንም አይሆኑም። ለዛ ነው ለተፈጥሮ ተስማሚ በሆኑ ምርቶች ልንተካቸው ይገባል የምንለው።"
ሌላው ሪል ብራንድስ የተሰኘ፣ ለአካባቢ ተስማሚና አስተማማኝ በሆኑ ምርቶች የማሸግ ስራ የሚሰራ ድርጅት ካለፈው ግንቦት ወር አንስቶ በሳምንት ከሚሊዮን በላይ የፊት መሸፈኛ ፕላቲኮችን ማምረት ጀምሯል። የድርጅቱ መስራች የሆኑት ኢያን ቤትስ ድርጅታቸው የሚያመርቷቸው ለኮሮና ቫይረስ መከላከያነት የሚውሉት የፊት መሸፈናዎች ለተፈጥሮ ተስማሚ ከሆኑ ቁሳቁሶች እንደተሰሩ ያስረዳሉ።
"ሙሉ ለሙሉ በቀላሉ ሊበሰብሱ ከሚችሉና ለረጅም ግዜ ሊቆዩ ከሚችሉ ቁሳቁሶች ነው የምንሰራቸው። ለምሳሌ ፊትን የሚሸፍነው ክፍል ከዛፍ ከሚገኝ ቃጫ ነው የሚሰራው። መጨረሻ ላይ እንዴት አስተላላፊ መስታወት ሆኖ እንደሚወጣ እራሱ አስገራሚ ሂደት ነው። የኮፍያውን ክፍል ደግሞ ለአጠቃቀም ምቹ በሆን ሁኔታ ከካርቶን ነው የምንሰራው። ስለዚህ ከእሽጉ ሲወጣ ምንም አይነት የመገጣጠም ስራ ሳይኖረው በቀጥታ ጭንቅላት ላይ ማጥለቅ ነው። "
ሪል ብራንድስ በቅርቡ ጋዎኖችንና የእጅ ጕንቶችንም ማምረት እንደሚጀምር ቤትስ ያስረዳሉ። ልክ እንደ ሪል ብራንድስ እንግሊዝ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ካምፓኒዎችም ዘላቂ ጥቅም መስጠት የሚችሉ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ምርቶችን ወደማምረት ፊታቸውን እያዞሩ ነው። ከነዚህ አንዱ 'ኦሽን ቪዩ' የተሰኘ ደግመው ጥቅም ላይ የሚውሉ "VP195" የተሰኙ
የፊት መሸፈኛ ጭምብሎችን የሚያመረተው ድርጅት ነው። የድርጅቱ የስራ ሂደት ሀላፊ ኒኮል ማክደርሞት፣ በሶስት ደረጃ የሚሰሩት የፊት ማስኮች እስከ 30 ጊዜ መታጠብ ይችላሉ።
"አሁን የምናረጋቸው የፊት ማስኮች አንድ ግዜ፣ አንድ ቀን ብቻ አርገን የምንጥላቸው መሆኑ እብደት ይመስለኛል። ልክ ቁምሳጥናችን ውስጥ ያሉ በየግዜው የምንለብሳቸውን ልብሶች አንድ ግዜ እየለበሱ እንደመጣል ማለት ነው። ይሄ ዘላቂነት የለውም።"
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያወጣው ሪፖርት በየእለቱ እየተጠቀምን የምንጥላቸው ራስን ከኮሮና ቫይረስ መከላከያ ግብዓቶች በየአመቱ ወደ ውቅያኖሶች ውስጥ የሚገቡትን 13 ሚሊዮን ቶን የሚሆኑ የፕላስቲክ ምርቶች የበለጠ እንዲጨምሩ ሊያደርግ እንደሚችል ያሳያል።