በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በደቡብ ኢትዮጵያ የፆታ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችና ህፃናት ፍትህ ይፈልጋሉ


 የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መዛመትን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶች ማሻቀብ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኗል። በቤት ውስጥ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶች መባባስ እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ ከኖሩት ጎጂ ባህላዊ ልማዶች መሃል የሆኑት ጠለፋና በለጋ እድሜ የሚፈፀሙ ጋብቻዎችም በደቡብ ክልል በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ መሆናቸውን የክልሉ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ አልማዝ ከፍታው ገልፀዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ የፆታ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችና ህፃናት ፍትህ ይፈልጋሉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:31 0:00


በደረሰባት ፆታዊ ጥቃት ምክንያት ስሟን መግለፅ የማትፈለገው የ21 አመት ወጣት፣ ትውልዷና እድገቷ በደቡብ ክልል፣ ከቀድሞው ሲዳማ ዞን፣ ጭሬ ወረዳ ወጣ ብላ በምትገኝ የገጠር ከተማ ነው። የ15 አመት ልጅ እያለች የስምንተኛ ክፍል ሚኒስ ትሪ መፈተኛ ፎቶ ለመነሳት ወደ ጭሬ ከተማ ከጏደኛዋ ጋር በሄደችበት ወቅት በደረሰባት ጠለፋ ምክንያት ከአንድ ወር በላይ ጠላፈዋ ጫካ ውስጥ እያሳደረ ተደጋጋሚ የወሲብና አካላዊ ጥቃት እንዳደረሰባት የምትናገረው ወጣት እስካሁን ፍትህ እንዳላገኘችም ታስረዳለች።

በደቡብ ክልል ጠፍቶ የነበረው ይህ አይነቱ ጠለፋና አስገድዶ ጋብቻ አሁን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሴቶችና ህፃናት እቤት መዋላቸውን ተከትሎ በድጋሚ መታየት መጀመሩንና ቁጥሩም እየጨመረ መሄዱን የክልልሉ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ አልማዝ ክፍታው ገልፀዋል።

ያናገርናት የጠለፋ ጥቃት የደረሰባት ወጣት፣ ጫካ ውስጥ በተራ ይጠብቁኝ ነበር ከምትላቸው የጠላፊዋ ጉዋደኞች እና ዘመዶች አምልጣ ለፖሊስ ብታመለክትም ሊረዷት ባለመቻላቸው ሀዋሳ እንደመጣችና በክልሉ የሴቶችና ህፃናት ቢሮ እርዳታ ይርጋለም ወደሚገኘው ጣሊታ ደጋፊ ያጡ ልጃገረዶች፣ አረጋውያንና ህፃናት ደጋፊ በጎ አድራጎት ድርጅት እንደወሰዷት ትናገራለች።

በመጠለያው ከማሳደግ ባሻገር ትምህርቷን ተምራ እንድትጨርስ የረዷት የጣሊታ ድርጅት መስራች ወይዘሮ አትክልት ጃንካ እንደሚያስረዱት ላለፉት 7 አመታት ለወጣትዋ ፍትህ ለማግኘት የተደረገው ጥረት ተስፋ አስቆራጭ ነበር።

ወይዘሮ አትክልት የተለያዩ ፆታዊ ጥቃት ደርሶባቸው ፍትህ ያላገኙ ሌሎች ሴቶችና ህፃናትንም ይርጋለም በሚገኘው መጠለያቸው ውስጥ ይረዳሉ። በተለይ የኮሮና በሽታን ተከትሎ ሴቶችና ህፃናት እቤት በመዋላቸው በሲዳማ ዞን የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶች መጨመሩን የሚያስረዱት ወ/ሮ አትክልት፣ ከሁለት ወራት በፊት በአሳደጋት አባቷ ተደፍራ ነፍሰ-ጡር የሆነች የ15 አመት ልጅ እሳቸው ጋር እንደምትገኝ፣ ደፋሪዋን ግን ለፍርድ ማቅረብ እንዳልተቻለም ይገልፃሉ።

አሁን ክልል በሆነው የቀድሞው ሲዳማ ዞን አካባቢ ሴቶች ልጆችና ህፃናት ጥቃት ተፈፅሞባቸው ፅንስ ከተፈጠረ በአካባቢው ባህል መሰረት ሴቶቹን ለጋብቻ የሚፈልጋቸው ስለማይኖር እናቶች የተወለዱትን ልጆች እንደሚጥሉም ወይዘሮ አትክልት ይገልፃሉ።

የክልሉ ሴቶችና ህፃናት ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ አልማዝም በኮሮና ምክንያት በክልሉ የሚፈፀሙ ፆታዊ፣ አካላዊና የስነልቦና ጥቃቶች መጨመራቸውን በጥናት ማረጋገጣቸውንና ጥናቱ በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ግልፀው፣ በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ያለውን የፍትህ መጏደል ለመቅረፍ ቢሮአቸው ከፍትህ አካላትና ጤና ቢሮ ጋር እየሰራ መሆኑን ያስረዳሉ።

በመግቢያችን ላይ የሰማችኃትና በጠለፋ ምክንያት ፆታዊና አካላዊ ጥቃት የደረሰባት ወጣት ለአመታት ፍትህ ባለማግኘቷና በጠላፊዋ የግድያ ዛቻ ምክንያት ተወልዳ ወደአደገችበትና ጠላፊዋ ወደሚኖርበት አካባቢ ተመልሳ መሄድ አልቻለችም። በዚህም ምክንያት እናትና አባቷን ላለፉት ሰባት አመታት ማየት እንዳልቻለች ትገልፃለች።

በፍትህ አካላት ዘንድ ከሚታዩ የፍትህ መጏደሎች በተጨማሪም ጥቃት ሲደርስ በአገር ሽማግሌዎችና በሀይማኖች አባቶች አማካኝነት ለመጨረስ የሚደረጉ አካሄዶችም እንዳሉ የገለፁት የደቡብ ክልል የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ቢሮ ሀላፊ፣ ይህን ለማረም ወጥ አሰራሮችን እስከቀበሌዎች ድረስ ለማውረድ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

XS
SM
MD
LG