በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ በተተኮሰበት ጥይት ሕይወቱ ማለፉን ፖሊስ አረጋገጠ


አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ
አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ

አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ዛሬ ማምሻውን ባልታወቁ ሰዎች መገደሉን በቦታው የሚገኙ ምንጮች ገለፁ።

አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ዛሬ ማምሻውን ባልታወቁ ሰዎች በተተኮሰ ጥይት መገደሉን በቦታው የሚገኙ ምንጮች ለአሜሪካ ድምፅ ገልፀዋል። የአርቲስቱ ሕይወት ማለፍ ከተሰማ በኋላ “ለቡስታር” በተሰኘ ሆስፒታል ተገኝተው ሕይወቱ ማለፉን ያረጋገጡት ምንጮች አርቲስት ሃጫሉ በጥይት የተመታው ከምሽቱ 3፡30 ገደማ ገላን እየተባለ በሚጠራው ኮንደሚኒየም አካባቢ እንደሆነ ገልፀዋል።

ማምሻውን ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው መረጃው ለፖሊስ ከደረሰ ጀምሮ ክትትል ሲደረግ እንደነበር ገልፀው፤ እስካሁን የተወሰኑ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ተናግረዋል።በድርጊቱ ውስጥ የተሳተፉትን ሰዎች ለመያዝ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል። አርቲስት ሃጫሉ ባለትዳርና የሁለት ሴት ልጆች አባት ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት ሐዘናቸውን ገለፁ
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በታዋቂው የኦሮሚኛ ቋንቋ ሙዚቀኛ ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት የተሰማቸውን ሐዘን ገለፁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት የሐዘን መግለጫ “ውድ ህይወት አጥተናል” ብለዋል።
አያይዘውም “የዚህ ድንቅና አንፀባራቂ ወጣት አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሕይወት መቀጠፍ ከተሰማ ጀምሮ በከባድ ሐዘን ውስጥ ለምንገኝ ሁሉ መፅናናትን እመኛለሁም” ብለዋል።
“የዚህን ክፉ ድርጊት ሙሉ የፖሊስ ምርመራ ሪፖርት እየተጠባበቅን እንገኛለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የድርጊቱን መጠን በመረዳት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚከናወኑ እንቅስቃሴዎች ትኩረት ሰጥተው እንደሚከታተሉም በጹሑፍ አስፍረዋል።
“ሐዘናችንን ራሳችንን በመጠበቅ እና ተጨማሪ ወንጀልን በመከላከል እንግለፅ ሲሉም አሳስበዋል።(ፎቶ ማኅበራዊ ሚዲያ)
(ተጨማሪ መረጃዎችን ከፖሊስ ለማጣራት ሙከራ እያደረግን ነው እንዳገኘን ይዘን እንመለሳለን።)

XS
SM
MD
LG