በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

‘እነሆ ለልጆች’ - በኃይሉ ገ/እግዚአብሔር


በኃይሉ ገ/እግዚአብሔር
በኃይሉ ገ/እግዚአብሔር

ህፃናት በስነ-ምግባር ታንፀው አድገው ነገ በሀገራዊና በራሳቸው ጉዳይ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ከትምህርት ቤት በቀጥታ ከሚቀስሙት ትምህርት ባሻገር፣ ከመፃህፍት፣ ፊልሞችና ከመገናኛ ብዙሃን የሚያገኟቸው መልእክቶች ትልቅ ሚና አላቸው። በተለይ ታሪክን ለልጆች በማስተማርና ማህበራዊ እሴቶችን በማስተላለፍ ረገድ ደግሞ ተረቶች ትልቅ ቦታ ይሰጣቸዋል።

‘እነሆ ለልጆች’ - በኃይሉ ገ/እግዚአብሔር
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:38 0:00

ህፃናት በስነ-ምግባር ታንፀው አድገው ነገ በሀገራዊና በራሳቸው ጉዳይ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ከትምህርት ቤት በቀጥታ ከሚቀስሙት ትምህርት ባሻገር፣ ከመፃህፍት፣ ፊልሞችና ከመገናኛ ብዙሃን የሚያገኟቸው መልእክቶች ትልቅ ሚና አላቸው።

በተለይ ታሪክን ለልጆች በማስተማርና ማህበራዊ እሴቶችን በማስተላለፍ ረገድ ደግሞ ተረቶች ትልቅ ቦታ ይሰጣቸዋል። የዛሬው እንግዳችን በኃይሉ ገ/እግዚአብሔር እነዚህን ተረቶችንና ትረካዎችን ለህፃናት በሚመች መልኩ በምስል እያቀናበረ የሚያቀርብ አዲስ የዩቲዩብ ቻናል ከፍቷል፣ ስለ ቻናሉና በህፃናት ዙሪያ ስለሚሰራቸው ስራዎች ከባልደረባችን ስመኝሽ የቆየ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ይህ በመግቢያው ላይ የሰማችሁት ተረት የተቀነጨበው በቅርብ ጊዜ ከጀርመን የባህል ተቇም ጋር በመተባበር ለህፃናትና ታዲጊዎች ልዩ ልዩ ትረካዎችንና ተረቶችን ከምስል ጋር አቀናብሮ በዩቲዩብ ቻናል አማካኝነት ማቅረብ ከጀመረው 'እነሆ ለልጆች' ቻናል ነው።

የዩቲዩብ ቻናሉን የከፈተው ደግሞ ከዚህ በፊት በተለያዩ መፅሃፎቹ፣ የህፃናት የቲያትር ድርሰቶቹና፣ ግጥምን በጃዝ በሚያቀርቡ ዝግጅቶች ላይ ዘና በሚያደርጉ ወጎቹ የምናውቀው በኃይሉ ገ/እግዚአብሔር ነው። በኃይሉን ከ 3 እስከ 12 አመት እድሜ ክልል ላሉ ላሉ ልጆ የተዘጋጀውን ይሄን እነሆ ለልጆች' የተሰኘ የዩቲዩብ ቻናል ለምን እንደጀመረ ጠይቀነው ነበር።

የአማርኛ ስነ-ፅሁፍ ምሩቅ የሆነውና ከዚህ በፊት 'ኑሮና ፖለቲካ' እንዲሁም 'መንታ መልኮች' በተሰኙት ለአዋቂዎች ባሳተማቸው መፅሃፎቹ እንዲሁም በግል የፕሬስ ውጤቶች ላይ በሚፅፋቸው መጣጥፎች ይበልጥ የሚታወቀው በኃይሉ፣ የጀርመን የባህል ማእከል ተቋም የልጆች መፅሃፍ አርታኢ ሆኖ ከመስራቱ በተጨማሪ፣ ከተቋሙ ጋር በመተባበር የህፃናት ቲያትሮችን እየፃፈ በእምቢልታ ሆቴል ያሳይ ነበር። ሁለት የህፃናት መፅሃፎችንም አሳትሟል።

በኢትዮጵያ የሚኖሩ ህፃናት በየቋንቋቸው በመማራቸው ምክንያት አንድ የሚያደርጉዋቸው ተመሳሳይ ታሪኮች እየሰሙ አይደለም የሚለው በኃይሉ ህፃናት በተለያየ ቇንቇም ቢሆን ተመሳሳይ ተረቶችና ታሪኮችን እንዲሰሙ በማድረግ አንድነት መፍጠር፣ ፍቅርን፣ መተሳሰብና ወንድማማችነትን በተረትና በጨዋታ ማስተማር ይቻላል ብሎ ያምናል። ተመሳሳይ ታሪኮችን በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ለማሳተምም ጥረት እያደረገ ነው።

በቀደመው ትውልድ የበርካታ የስነ-ፅሁፍ ውጤቶች ባለቤት የሆኑት ደራሲ ከበደ ሚካኤል ተረቶችን በግጥም ቅርፅ እያደረጉ እንደ ፋኖስና ብርጭቆ ፣ አውራ ዶሮና የአይጥ ግልገል እንዲሁም ብረት ድስትና ሸክላ ድስት የመሳሰሉ ትምህርት አዘል ፅሁፎችን ለልጆች ያቀርቡ ነበር። ለዚህ ትውልድ ግን እንደነዚህ አይነት የልጆችን ስብዕና የሚያንፁ የግጥም ተረቶች እየቀረቡ አይደሉም የሚለው በኃይሉ፣ በዚህ ዙሪያ ብዙ ስራ መስራት እንደሚፈልግም ይናገራል።

አሁን የሰማችሁት ድግሞ 'እነሆ ለልጆች' ዩቲዩብ ቻናል ላይ ከሚቀርቡት ዝግጅቶች መሃል 'ከእኛ ቤት ለእናንተ' በሚል ርዕስ ከተሰኘው የተቀነጨበ ነው። ዝግጅቱ እማዋይሽ ስሜ የተሰኘች የበኃይሉ ባልደረባ ከልጆቿ ጋር፣ በተለይ በኮሮና ምክንያት ከቤት መውጣት በማይመከርበት ጊዜ፣ አትክልት ሲንከባከቡ፣ መፅሃፍት ሲያነቡ ወይም የቤት እንስሳትን ንፅህና ሲጠብቁ በማሳየት ልጆች እንዲማሩ የሚያደርግ ነው። ዛሬ የምንሰጣቸውን ነው ነገ ልጆች ላይ የምናየው የሚለው በኃይሉ፣ ከተረቶቹ በተጨማሪ እንደነዚህ አይነት ዝግጅቶች ለልጆች የወደፊት ስነ-ምግባር መሰረት በመሆናቸው የበለጠ መስራት ይጠበቅብናል ይላል።

'እነሆ ለልጆች' ዩቲዩብ ቻናል ገና የጅምር መንገድ ላይ ነው። በአዛውንቶች የሚተረኩ ተረቶችንና በህፃናት በራሳቸው የሚዘጋጁ ዝግጅቶችን ጨምሮ እራሱ የጻፋቸውና ገና ለህትመት ያልበቁ ተረቶቹ በምስል እንዲቀናበሩ ማድረግ በኃይሉ በዩቲዩብ ቻናሉ ሊሰራቸው ከሚያስባቸው ስራዎች ጥቂቶቹ ናቸው። በህፃናት ዙሪያ በቂ ስራ አልተስራም የሚለው በኃይሉ ነገ አገሩን የሚወድ ብቁ ዜጋ ለማፍራት ዛሬ ተባብረን እንስራ ሲል ተመሳሳይ ፍላጎትና ሙያ ያላቸው ሌሎች ሰዎች የነገው ትውልድ በስነ-ፅሁፍ ለማነፅ አብረውት እንዲሰሩ ጥሪ ያቀርባል።

XS
SM
MD
LG