በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

26 ሚሊዮን ተማሪዎች እቤታቸው ተቀምጠዋል


Students walk home from school in the outskirts of Badme, territorial dispute town between Eritrea and Ethiopia currently occupied by Ethiopia, June 8, 2018.
Students walk home from school in the outskirts of Badme, territorial dispute town between Eritrea and Ethiopia currently occupied by Ethiopia, June 8, 2018.

የኮሮና ቫይረስ በማህበረሰቡ ውስጥ ሊያስከትል የሚችለውን የጤና ደህንነት በመፍራት ኢትዮጵያ እንደ አብዛኞቹ የዓለም አገራት ትምህርት ቤቶችን በመዝጋቷ፣ በአሁኑ ሰአት 26 ሚሊዮን የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በቤት ውስጥ እንደሚገኙና ይህም በመማር ማስተማሩ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንዳለው የትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል።

26 ሚሊዮን ተማሪዎች እቤታቸው ተቀምጠዋል
please wait

No media source currently available

0:00 0:10:16 0:00


የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው ወላጆችም ተማሪዎች በየቤታችቸው ሆነው ትምሕርት እንዲከታተሉ መደረጋቸው የኅብረተሰብን ጤና በመጠበቅ በኩል አማራጭ የሌለው መፍትሔ ቢሆንም ፤ ተገቢውን እውቀት በማስተላለፍ በኩል ግን ተጽኖ እያሰደረ ነው ይላሉ።

በኮሮና ቫይረስ የተያዘው የመጀመሪያው ሰው ከተገኘና በዓለም ያለው ስጋት ወደ ኢትዮጵያም ከተጋባ በኃላ መንግስት በመጀመሪያ የወሰደው እርምጃ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ከየቤታቸው ሆነው እንዲከታተሉ ማድረግ ነው። ይህ እርምጃ ተገቢ መሆኑን የሚያምኑበት ወላጆች፣ በዚህ መሰረት በቤት ውስጥ ልጆቻቸውን በማስተማር ላይ እንደሚገኙ ገልፀው የመማር ማስተማር ሂደቱ ግን ተግዳሮቶች አሉት ይላሉ።

የሰባት አመትና የአራት አመት ልጆቻቸውን 'One Planet International' በተባለ የግል ትምህርት ቤት የሚያተምሩት ወይዘሮ ፍቅረሰላም ጌትነት፣ ከስራቸው ተጨማሪ ልጆቻቸውን በቤት ውስጥ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማድረግ በጣም ከባድ ነው ይላሉ።

የዘጠኝ አመት ልጃቸውን ፊውቸር ሆፕስ በተባለ ሌላ የግል ትምህርት ቤት የሚያስተምሩትና የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ሙላትወርቅ መኮንንም የተማሪዎች በቤት ውስጥ ትምህርት መከታተል በትምህርት አቀባበላቸውና በስነምግባራቸው ላይ ተፅእኖ እንደሚያሳድር ይገልፃሉ።

አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ደህረ-ግፆችን፣ የቴሌግራም ቻናሎችንና ወርክሽቶችን በመጠቀም፣ እንዲሁም ከወላጅ ጋር በየጊዜው በመነጋገር ተማሪዎች ከቤታቸው ሆነው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ጥረት እያደረጉ ነው። በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የሽመልስ ሀብቴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ሐጎስ እንደገለፁልን ግን፣ በትምህርት ቤቱ የሚማሩ ተማሪዎች ካለባቸው የአቅም ውስንነት አንፃር በድህረ-ገፆች ላይ የሚሰጡ ንባቦችን የሚከትተሉ ተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ ነው። አቶ ዝናቡ ጨምረው በኮርኖና ቫይረስ የተጠረጠሩ ሰዎች ለይቶ ማቆያነት ከተመረጡ ቦታዎች መሁል አንዱ ሽመልስ ሀብቴ በመሆኑ በአሁኑ ሰአት ትምህርት ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ያለው ወደ 30 የሚጠጉ ክፍሎችን ለዛ ማዘጋጀት ላይ ነው።

በግል ትምህርት ቤት ውስጥ በሚማሩ ተማሪዎች መሀከልም ከፍተኛ ልዩነት እንዳለ የገለፁልን ደግሞ የ 'One Planet International' ርዕሰ መምህር የሆኑት ጀማል ኢብራሂምም ናቸው። አቶ ጀማል አክለውም በተለይ በአብዛኛው የገጠር አካባቢዎች የሚገኙ ሴት ተማሪዎች ብዙ ተግዳሮት ያለባቸው ከመሆኑ አንፃር፣በዚህ ወቅት ትምህርታቸውን ለመከታተል አዳጋች ይሆንባቸዋል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልፃሉ።

በዚህ ጉዳይ ያነጋገርናቸው የትምህርት ሚኒስቴር ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሀላፊ ወይዘሮ ሐረጏ ማሞ፣ በአሁኑ ሰአት 26 ሚሊዮን የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በቤታቸው እንዳሉ ገልፀው ትምህርት በሬዲዮ፣ በፕላዝማ ቴሌቭዥን፣ በዩቲዩብና በቴሌግራም ለማዳረስ እየተደረገ ያለው ጥረት ግን ሁሉንም ተደራሽ አረጏል ማለት እንደማይቻል ያስረዳሉ።

ወይዘሮ ሀረጏ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በመማር ማስተማሩ ላይ እያደረሰ ያለውን ተፅእኖ ከግምት ውስጥ በማስገባት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት በሚመለሱበት ወቅት በሁሉም የግልና

የመንግስት ትምህርት ቤቶች የማካካሻ ትምህርት ሊሰጥ እንደሚገባና ለዚህም ዝግጅቶች እንደሚደረጉ ገልፀዋል። ሀገር አቀፍ ፈተና እና የመሳሰሉት ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተም ቫይረሱ ተወግዶ መደበኛ የመማር ማስተማሩ ሂደት ሲቀጥል ሊካሄድ የሚችልበትን ቅድመ ሁኔታዎች ኮሚቴ አቇቁመው እየሰሩበት ምሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ከ700 ሺሕ በላይ ከሚሆኑት የከፍተኛ ትምሕርት ተቃማት ተማሪዎች ወስጥ 200 ሺሕ የሚሆኑት የሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ብቻ በኦንላይን ትምሕርታቸውን እየተከታተሉ መሆኑን የገለፁልን ደግሞ በሳይንስ እና ከፍተኛ ትምሕርት ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮ ዳይሬክተር አቶ ደቻሳ ጉርሞ ናቸው።

የትምህርት ሚኒስቴር ሀላፊዎቹ አለምን ያስጨነቀው አለም አቀፍ ወረርሽኝ ጉዳቱ በሁሉም ዘርፍ በመሆኑ በትምህርት ላይ ያሳደረውን ክፍተት ለመሙላት ትምህርት በሚጀመርበት ጊዜ ተማሪዎች በቂ ትምህርት እንዲያገኙ ይደረጋል፣ እስከዛው ግን ተማሪዎች ከትምህርታቸው የመቆራረጥ ስሜት እንዳይፈጠርባቸው በቻሉት አቅም መፅሀፎቻቸውን በማንበብና ትኩረታቸውን ትምህርት ላይ በማድረግ የራሳቸውን ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ይመክራሉ።

XS
SM
MD
LG