በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ነፍሰጡር እናቶች የህክምና ክትትል ቀንሷል


Ethiopiaon doctors attend training to use mechanical ventilators for COVID-19 patients at the American Medical Center (AMC) in Addis Ababa, Ethiopia, on April 1, 2020. (Photo by Michael Tewelde / AFP)
Ethiopiaon doctors attend training to use mechanical ventilators for COVID-19 patients at the American Medical Center (AMC) in Addis Ababa, Ethiopia, on April 1, 2020. (Photo by Michael Tewelde / AFP)

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት አብዛኛው የጤና ተቋማት የእርግዝና ጊዜአቸው ገና የሆኑትንና ተጨማሪ የጎንዮሽ ችግር የሌለባቸውን እናቶች ቀጠሮ እንዲራዘም አድርገዋል። ይህን ተከትሎ አንዳንድ ነፍሰጡር እናቶች በተሳሳተ ግንዛቤ ወደ ጤና ተቃማት ለክትትል መሄድ ፍርሀት እንዳሳደረባቸውና አንዳንዶቹም ሙሉ ለሙሉ ክትትል በማቇረጣቸው ለችግር እየተጋለጡ መሆናቸውን የህክምና ባለሙያዎች ይገልፃሉ። በዚህም ምክንያት ለተጨማሪ የጤና እክል የሚጋለጡ እናቶች ተበራክተዋል።

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ነፍሰጡር እናቶች የህክምና ክትትል ቀንሷል
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:47 0:00


የአምስት ወር ነፍሰ ጡር የሆነችው ማርታ ጌታቸው የዛሬ አራት አመት የመጀመሪያ ልጇን ከመውለዷ የበፊት የነበረውን የእርግዝና ጊዜዋን ክትትል ታደርግላት ከነበረችው ሀኪሟ ጋር በቅርብና ቶሎ፣ ቶሎ ትገናኝ እንደነበር ታስታውሳለች። ከመደበኛ ስራዋም በተጨማሪም በግሏ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ እና ከቤተሰብና ጉዋደኛ ጋር እንደልብ በመገናኘት ታሳልፍ ነበር።

በዚህ በሁለተኛው እርግዝናዋ ግን ብዙ ነገር ተቀይሯል። ኮሮና ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ ሆስፒታሎች ለእርጉዝ እናቶች የሚደረጉ የክትትል ቀጥሮዎችን በማራዘማቸው ማርታ እንደቀድሞው ከሀኪሟ ጋር ቶሎ ቶሎ አትገናኝም። በተለይ ኮሮና በገባበት የመጀመሪያ ሳምንታት ሆስፒታል መገኘት በራሱ ያስፈራ ነበር ትላለች።

ማርታ ስለበሽታው እያወቀችና እንዴት መጠንቀቅ እንዳለባት ባወቀች ቁጥር ግን ፍርሀቷ እየለቀቃት መሄዱን ትናገራለች። የማርታ ፍራቻ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አለምን በሚያምስበት ወቅት እርጉዝ የሆኑ እናቶች ሁሉ ፍራቻ ከሆነ ሰነባበት። ይህን ተከትሎ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በሆስፒታል ክትትል የሚያደርጉ እናቶች ቁጥር በእጅጉ መቀነሱን የገለፁልን በቅዱስ ጳውሎስ ሜዲካል ኮሌጅ የማህፀንና ፅንስ ህክምና ትምህርት ሀላፊ ዶክተር ታደሰ ኡርጌ ናቸው።

የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ መግባቱ በተረጋገጠበት መጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ጀምሮ የጤና ተቋማት የእርግዝና ጊዜአቸው ገና የሆኑትንና ተጨማሪ የጎንዮሽ ችግር የሌለባቸውን እናቶች ቀጠሮ እንዲራዘም አድርገዋል። ነገር ግን አንድ አንድ እናቶች በተራዘመላቸውም ቀጠሮ ባለመገኘታቸው ችግር ገጥሟቸው ተጨማሪ ህክምና ያስፈለጋቸው እናቶች በተደጋጋሚ እንዳጋጠማቸው ዶክተር ታደስ ይገልፃሉ።

በተመሳሳይ በጎንደር ከተማና በዙሪያው ላሉ ወረዳዎች አገልግሎት በሚሰጠው የጎንደር ዩንቨርስቲ ሆስፒታል ክትትል የሚያደርጉ ነፍሰጡር እናቶች ቁጥም በግማሽ መቀነሱን የዩንቨርስቲው የማህፀንና ፅንስ ትምህርት ክፍል ሀላፊ ዶክተር ዘላለም መንግስቱ ይናገራሉ። ክትትል የሚያደርጉ እናቶች ቁጥር በዚህ ደረጃ መቀነስ ምክንያቱ በኮሮና ቫይረስ ፍራቻ ብቻ ነው የሚያስችል ጥናት አለመኖሩን የሚያስረዱት ዶክተር ዘላለም፣ ወረርሽኙን ተከትሎ ሆስፒታሉ ያደረጋቸው የአሰራር ለውጦችም ለመቀነሱ አስተዋኦ አርጏል ይላሉ።

በጎንደር ዩንቨርስቲ ሆስፒታል ለክትትል የሚመጡ ነፍሰጡሮች ቁጥር በዚህ መጠን ይቀንስ እንጂ፣ በሆስፒታሉ የሚወልዱ እናቶች ቁጥር ግን በዚህ ወቅት መጨመር አሳይቷል የሚሉት ዶክተር ዘላለም፣ ከወረርሽኙ ድንገተኝነት አንፃር ሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያዎች ራሳቸውን ከበሽታው ለመጠበቅ የሚያስፈልጋቸው የህክምና ግብዓቶች በበቂ ሁኔታ እየቀረበላቸው ባይሆንም፣ ለመደበኛ አገልግሎት ይጠቀሙባቸው የነበሩትን ግብዓቶች በመጠቀም እናቶችንም ሆነ ሌሎች ታካሚዎችን ከወረርሽኙ ለመጠበቅ ሆስፒታሉ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ያረጋል ይላሉ።

የኮቪድ-19ን ወረርሽኝን ፍራቻ በጤና ተቇማት ክትትል የሚያደርጉ ነፍሰጡር እናቶች ቁጥር መቀነስ ያሳሰበው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶች፤ ሕጻናትን እና ጨቅላ ሕጻናትን ጤና አገልግሎት ማስቀጠል በየትኛውም ሁኔታ ቢሆን ወደኋላ የማይባል የጤናው ሴክተር ዋና ተግባር መሆኑን ገልፆ እናቶች ወደ ህክምና ተቋማት በመሄድ እርግዝናቸውን እንዲከታተሉ ጥሪ አቅርቧል።

አንዴ ከተከሰቱ በኃላ የማንመልሳቸው ችግሮች አሉ የሚሉት ዶክተር ታደሰ ገና ለገና ኮሮና ቫይረስ ይይዘኛል በማለት ራስን ለገዳይ ችግር ማጋለጥ ተገቢ አይደለም፣ የጤና ተቋማትም ባላቸው አቅም የዚህን በሽታ ለመከላከል የሚያስፈልገውን ነገር አድርገው ነው የሚጠብቁት ይላሉ።

ማርታም ክትትል በምታደርግበት አይሲኤምሲ ሆስፒታል የምታየው ጥንቃቄ ያለፍርሀት ክትትሏን እንድትቀጥል እንደረዳት ገልፃ ሌሎችም ነፍሰጡር እናቶች ክትትላቸውን እንዳያቇርጡ ትመክራለች።

በተለይ የእርግዝና ወራቸው እየቀረበ ያሉና ከእርግዝና በፊትም ሆነ በእርግዝና ወቅት ተጏዳኝ የጤና ችግር ያለባቸው እናቶች ክትትል ማቇረጥ የለባቸውም የሚሉት የጤና ባለሙያዎቹ የእናቶችና የህፃናትን ሞት ማስቀረት የሚቻለው እናቶች ተገቢውን ክትትል አርገው በጤና ተቇማትና በባለሙያዎች አማካኝነት እንዲሆን ያሳስባሉ።

XS
SM
MD
LG