በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በኢትዮጵያ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች በእጥፍ ሊያድግ ይችላል


በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በኢትዮጵያ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች በእጥፍ ሊያድግ ይችላል
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በኢትዮጵያ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች በእጥፍ ሊያድግ ይችላል

የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከቀጠለ በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው 15 ሚሊዮን ሰዎች በተጨማሪ ሌላ 15 ሚሊዮን ሕዝብ ለምግብ እጥረት ሊጋለጥ ይችላል ሲሉ በግብርና ሚኒስቴር እርሻ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ ለቪኦኤ ገለፁ።

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በኢትዮጵያ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች በእጥፍ ሊያድግ ይችላል
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:04 0:00

በአየር ንብረት መዛባት፣ የዘመናዊ አስተራረስ ዘዴዎች አለመኖር፣ ግብርናው በመስኖ ላይ የተመሰረተ ባለመሆኑና በአምበጣ መንጋ ወረርሽኞች ምክንያት በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ 15 ሚሊዮን ለምግብ እጥረት የተጋለጡ ሰዎች እንዳሉ የገልፁት አቶ ሳኒ፣ በኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ምክንያት ተጨማሪ አደጋ ላይ የሚወድቁትን ህዝቦች ጨምሮ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር በእጥፍ አድጎ ወደ 30 ሚሊዮን ከፍ ይላል የሚል ስጋት እንዳለ ጠቁመዋል።

አቶ ሳኒ አያይዘው የኮሮና ቫይረስ ከውጪ የሚገቡ የግብርና ምርት አቅርቦትና ስርጭት ላይም ተፅእኖ ማሳደሩን ገልፀዋል። ኢትዮጵያ ለዚህ አመት የሚያስፈልጋትን 14 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ መስከረም ላይ ግዢ ፈፅማ 12.5 ሚሊዮኑ ወደብ ላይ መድረሱንና 9.3 ሚሊዮኑ ደግሞ ሀገር ውስጥ መግባቱን የሚናገሩት ሚኒስቴር ዴኤታው፣ በወረርሽኙ ምክንያት እንቅስቃሴዎች በመገደባቸው ምክንያት ወደብ ላይ የቀሩትንም ሆነ ሀገር ውስጥ የገቡትን ለማጓጓዝ የተፈጠረውን የመስተጓጎል ችግር ለመፍታት ከትራንስፖርት ሚኒስቴርና ከደረቅ ጭነት ማህበራት ጋር በመሆን እየሰራን ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ የግብርና ምርት አቅርቦትና ፍላጎት ላይ እያደረሰ ያለው ተፅእኖ መታየት ጀምሯል ሲል በኢትዮጵያ የሚገኘው የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት ይገልፃል። የምግብና እርሻ ድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ ፋቱማ ሰይድ እንደገለፁልን ካለፈው አመት ሰኔ ወር ጀምሮ የሰብል ውጤቶችን እያጠቃ ከሚገኘው የአምበጣ መንጋና በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚከሰተው ድርቅ ያላገገመው የግብርና ምርትና የግብርና ውጤት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የዘንድሮ በ30 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ያብራራሉ።

ኢትዮጵያ በምግብ አቅርቦት እራሷን የቻለች አገር ባለመሆኗ በየአመቱ 20 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆን ስንዴ፣ ጥራጥሬና ዘይት ጨምሮ የተለያዩ የምግብ አይነቶችን ከውጪ ታስገባለች። እነዚህን የግብርና ግብዓቶች ለማጓጓዝ ካጋጠመው መስተጓጎል ባለፈ ኮሮና ቫይረስ እስካሁን በግብርናው ላይ የከፋ ተፅእኖ አላደረሰም የሚሉት አቶ ሳኒ ኢትዮጵያ ዘንድሮ ከውጪ ማስገባት የነበረባትና ያላስገባችው ምግብ የለም ይላሉ።

በዚህ ጉዳይ ያነጋገርናቸው በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን፣ አደአ ወረዳ አርሶአደር የሆኑት ገብሬ ዳዲ ዋቀዮ ወቅቱ የመኸር እርሻ የሚጀመርበት ጊዜ እንደመሆኑ ማረስ መጀመራቸውንና እስካሁን ባለው ሁኔታ የእርሻ ስራቸው አለምስተጓጎሉን ገልፀው፣ ገበሬው በኮሮና ቫይረስ የሚያደርገው ጥንቃቄ አለመኖሩ ግን እንደሚያሰጋቸው ይናገራሉ።

ላለፉት አስራ ሁለት አመታት ዘር የማባዛትና በአማራ ክልል ለሚገኙ 28 ሺህ ገበሬዎች የማከፋፈል ስራ የሚሰራው የባህርዳር እርሻ አገልግሎት ባለቤት ይማም ተሰማ በበኩላቸው ኮሮና ወደ ሀገር ውስጥ የገባው የዘር ማባዛት ስራ አልቆ በሚሰራጭበት ወቅት በመሆኑ ግብርናው ስራ ላይ እስካሁን የጎላ ተፅእኖ ባያደርስም ገበሬው ለበሽታው የሚያደርገው ጥንቃቄ ግን ብዙም አይደለም ይላሉ።

የኮሮና ቫይረስ ከብዙ አቅጣጫ ፈተና የማያጣው የኢትዮጵያ የምግብ ምርትና አቅርቦት ላይ የደቀነውን ስጋት ለመታደግ አርሶአደሩን በቫይረሱ ዙሪያ ግንዛቤ ከማስጨበጥ አንስቶ ቫይረሱ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሶ ምግብ ከውጪ ማስገባት የማይቻልበት ሁኔታ ቢፈጠር፣ በሀገር ውስጥ ምርት የምግብ አቅርቦት ማረጋገጥ የሚቻልባቻቸውን መንገዶች እየተጠኑ መሆኑን አቶ ሳኒ ረዲ ገልፀዋል። የአለም ምግብ ድርጅት በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት በአለም ላይ በረሀብ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር ወደ 265 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችልና በታዳጊ አገራት ጉዳቱ የበለጠ ሊሆን እንደሚችል ማስጠንቀቁ ይታወሳል።

XS
SM
MD
LG