በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ሚና


የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ሚና አብርሃም ወልዴ የባላገሩ ቴሌቭዥን ዋና ዳይሬክተር እና መላኩ ብርሃኑ የአርትስ ቴሌቭዥን ኦፕሬሽን ኃላፊ
የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ሚና አብርሃም ወልዴ የባላገሩ ቴሌቭዥን ዋና ዳይሬክተር እና መላኩ ብርሃኑ የአርትስ ቴሌቭዥን ኦፕሬሽን ኃላፊ

ለወራት የአለም ስጋት ሆኖ በቀጠለው የኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በኢትዮጵያም እያሻቀበ መሄዱን ተከትሎ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን፣ ግለሰቦች ሊያደርጏቸው ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች ከማስተማር ባለፈ ለወትሮው ማህበረሰቡ በአካል ተገኝቶ ይሳተፍባቸው የነበሩትን ማህበራዊና ሀይማኖታዊ ስነስርዓቶች ከቤታቸው ሳይወጡ ባሉበት እንዲከታተሉ አድርገዋል።

ለረጅም ጊዜ በሙከራ ስርጭት የቆየውና ዋናውን ስርጭት ከጀመረ ገና የሳምንታት እድሜ ያስቆጠረው ባላገሩ የቴሌቭዥን ጣቢያ ስርጭቱን የጀመረው ከኮሮና ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ለህዝብ በማድረስ ነበር።

የቴሌቭዥን ጣቢያው መስራች አባል እና ዋና ዳይሬክተር የሆነው አብርሀም ወልዴ እንደገልፀልን፣ አስቀድሞ በፋሲካ ሰሞን ዋናውን ስርጭቱን ለመጀመር አቅዶ የነበረው ባላገሩ የቴሌቭዥን ጣቢያ፣ የመላው ህብረተስብ ርብርብ በሚፈለግበት በዚህ ወሳኝ ወቅት እንደ ሚዲያ ተቇም የራሳችንን አስተዋፅኦ ማድረግ አለብን በሚል ውሳኔ የቴሌቭዥን ጣቢያው የሙከራ ስርጭቱ አቇርጦ ወደ ሙሉ ስርጭት እንዲሸጋገር ተደርጏል ይላል።

የኮሮና ቫይረስ እያስከተለ ካለው የጤና፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስ አንፃር ማህበራዊ ሚዲያዎችን ጨምሮ አጠቃላይ የመገናኛ ብዙሀን ለህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ የማቅረብና ሰዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ የማስተማር ሀላፊነት ተጥሎባቸዋል።

ሌላው ያነጋገርነውና ዘጠና በመቶ የመደበኛ ፕሮግራሙን በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ያሉ ባሉ ዘገባዎች የተካው ደግሞ አፍሪካን ሬኔሳንስ ቴሌቭዥን ሰርቪስ ወይም አርትስ ቲቪ የቴሌቭዥን ጣቢያ ነው። የጣቢያው ዋና ኦፕሬሽን ሀላፊ መላኩ ብርሀኑ እንደገለፀልን የኮሮና ቫይረስ እጅግ አሳሳቢ በመሆኑና አሁን ያለውን የተስፋ መስኮት ጠብቆ፣ በበሽታው ሌሎች አገሮች እንደተጠቁት ህብረተሰቡ እንዳይጠቃ የማድረግ ሀላፊነቱን ለመወጣት አርትስ ቴሌቭዥን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

የሚደርጉት ጥረቶች እንዳሉ ሆነው፣ አብርሀምን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሚዲያ ተቇማት ሚዛናዊ አቀራረብ ምን ይመስላል በሚል ላቀረብንለት ጥያቄ ሲመልስ የኮሮና ቫይረስ አዲስ ወረርሽኝ ከመሆኑ አንፃርና በበሽታው ዙሪያ ያሉ መረጃዎች በሙሉ ጥርት ያሉ አለመሆናቸው ሚዛናዊ ዘገባ ላይ ተፅእኖ አሳድሯል ይላል።

መላኩም በበኩሉ በአሁኑ ወቅት ሀሰተኛ ወይም የተዛቡ መረጃዎች፣ በተለይ በማህበረሰብ ሚዲያዎች ላይ መቅረባቸው ከበሽታው እኩል ህብረተስቡ ላይ ጉዳት የማስከትል አቅም አላቸው፣ ስለዚህ እንደዚህ ያሉ የተዛቡ መረጃዎችንም ለማጥራት እንሰራለን ይላል።

የአለም አቀፉ የምርመራ ጋዜጠኞች ትስስር ያለፈው ወር ላይ ጋዜጠኞች COVID 19ን በምን መልኩ መዘገብ አለባቸው በሚል ጠቃሚ ምክሮችን የያዘ ሪፖርት አውጥቶ ነበር። በሪፖርቱም ላይ ጋዜጠኞች እውንታንና ግምታዊ ሀሳቦችን እንዲለዩ፣ ትኩረት ለመሳብ ሲባል ዘገባዎችን አስፈሪ እንዳያደርጉና የሚያብራሩ ባለሙያዎችን በጥንቃቄ እንዲመርጡ መክሯል።

(ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ)

የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ሚና
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:48 0:00


XS
SM
MD
LG