በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆኑ


ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆኑ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆኑ

የኖርዌይ የኖቤል ሽልማት ኮሚቴው አሸናፊነታቸውን ይፋ ባደረገበት መግለጫ ፤ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ለሰላምና ለዓለም አቀፍ ትብብር ላደረጉት ከፍተኛ ጥረት የሽልማቱ አሸናፊ መሆናቸውን አብስሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሽልማቱን አስመልክተው በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት አጭር መልዕክት፤ "ይህ ሽልማት የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ነው" ብለዋል። በዚሁ አጭር መልዕክታቸው ላይ "ኖርዌይ የኖቤል ሽልማት ሰጪ ኮሚቴ ውሳኔ በጣም ተደስቻለሁ። ለሰላም ሲሉ ጠንክረው ለሚሠሩ ሁሉ ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ" ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የትዊተር ገፅ
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የትዊተር ገፅ

"ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር ዓቢይ አህመድ የ2019 የኖቤል ሠላም ሽልማትን አገኙ! እንኳን ደስ አሌት!እንኳን ደስ አለሽ እናት አገር ኢትዮጵያ! በአገራችን አራቱ ማዕዘን: በዓለም ዙርያ የምትኖሩ የዚች የተባረከች አገር ልጆች ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ" ያሉት ደግሞ ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ናቸው።

ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ
ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ

አምስት አባላት ያሉት የኖርዌይ የኖቤል ሽልማት ሰጪ ኮሚቴ ሰብሳቢ በርቲ ረኢስ አንደርሰን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሽልማቱን አሸናፊ መሆናቸውን ሲያበስሩ፤ አብይ አሕመድ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለ20 ዓመታት የነበረውን የድንበር ይገባኛል ውዝግብና አለመግባባት ሥልጣን በያዙ በወራት ጊዜ ውስጥ በመፍታት ሰላም አምጥተዋል። በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ቁርሾም በመፍታት ለእርቅና ለሰላም በማብቃታቸው የዘንድሮው የ2012 ኖቤል የሰላም ሎሬት ሆነው ተመርጠዋል።

NRC Secretary General Jan Egeland
NRC Secretary General Jan Egeland

ይህ ኮሚቴ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ለሽልማት ያበቋቸውን በጎ ተግባራት በዘረዘረበት ምዕራፍም “ አብይ ገና ወደ ሥልጣን በመጡበት በመጀመሪያው 100 የሥልጣን ቀናት በሀገሪቱ ላይ ተጥሎ የነበረውን አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ እንዲነሳ አድርገዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች ከእስር ተፈተዋል፣ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ተጥሎ የነበረው ቅድመ ምርመራ እንዲቀር ተደርጓል። በውጭ አገር ነበሩ የተቃዋሚ ፓርቲ ቡድኖች ወደ አገር ውስጥ ገብተው በሰላማዊ መንገድ የሚሠሩበትን ሁኔታ አመቻችተዋል፣ በሙስና ሲጠረጠሩ የነበሩ የወታደራዊ አመራሮችና ባለስልጣኖችን ከሥልጣን እንዲነሱ አድርገዋል እንዲሁም የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲጨምር አድርገዋል” ይላል።

የኖርዌይ የኖቤል ሽልማት ኮሚቴው አሸናፊነታቸውን ይፋ ያደረገበት መግለጫ
የኖርዌይ የኖቤል ሽልማት ኮሚቴው አሸናፊነታቸውን ይፋ ያደረገበት መግለጫ

በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደታየው ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አሕመድ ኦስሎ ከሚገኘው የኖቤል ሽልማት ቢሮ ከኮሚቴው ጸሐፊ ስልክ ተደውሎ ማሽነፋቸው በተነገራቸው ወቅት፤ “በጣም ነው የማመሰግነው ዜናውን ስሰማ ከፍተኛ ክብር እና መደናገጥ ተሰምቶኛል:: በጣም አመሰግናለው! ይህ ለአፍሪካ የተሰጠ ለኢትዮጵያ የተሰጠ ነው፡፡ ሌሎች የአፍሪካ መሪዎችም በአህጉራችን ላይ ሰላም ለማስፈን በትጋት እንደሚሠሩ ይታየኛል፡፡ በጣም አመሰግናለው፡ በጣም ተደስቻለሁ ደግሞም በዜናው ተደናግጫለሁ፡፡” ሲሉ ምላሽ ምላሽ ሰጥተዋል።

የኖቤል ሽልማት ኮሚቴው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአገሪቱ ጠንካራ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ለሚሠሩት ሥራም እውቅና ሰጠቷል። የበለጠ ደግሞ በኢትዮጵያና በኤርትራ የተካሄደው የሰላም ስምምነት ለሁለቱም አገሮች በጎ ለውጥን አስገኝቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከዚህ በተጨማሪ በምስራቅና በሰሜን አፍሪካ ሰላም ለማስፈን ያከናወኑት በጎ ተግባር በጉልህ የሚጠቀስ እንደሆነ ኮሚቴው አፅንኦት ሰጥቶታል። የኖቤል የሰላም ሽልማቱ ከዓለም አቀፍ እውቅናው በተጨማሪ 900 ሺሕ ዶላር የገንዘብ ሽልማትም አለው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ሽልማታቸውን በመጪው በመጪው ታኅሣሥ ወር ኦስሎ ተገኝተው ሽልማታቸውን ይወስዳሉ ተብሏል።

በተያያዘም የዓለም አቀፍ ታዋቂ የሰብዓዊ መብት ድርጅት መሪዎች፣ የአገር መሪዎች፣ አምባሳደሮችና ታዋቂ ሰዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የደስታ መግለጫ መልዕክት እያስተላለፉ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ “ብዙ ጊዜ የተስፋ ንፋስ በአፍሪካ እየነፈሰ ነው እላለሁ። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክኒያቴ አብይ አሕመድ ነው” ብለዋል። አያይዘውም “የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ራዕይ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ታሪካዊ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ አስችሏቸዋል። ባለፈው ዓመት ይህንን ስምምነት ሲፈራረሙ በቦታው በመኖሬ ደግሞ ክብር ይሰማኛል።” ሲሉ በመልካም ምኞት መግለጫው ላይ አስፍረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

ዋና ጸሐፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በመልዕክታቸው መጨረሻ፤ “ይህ አዲስ ምዕራፍም አካባቢው ደህንነትን እና መረጋጋትን የሚያሰፍን አዲስ ዕድሎችን ከፍቶለታል። እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በአመራርነታቸው ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እና ከአፍሪካ ውጭ ላሉ መሪዎችም ግሩም ምስሌ መሆን ችለዋል።” ብለዋል።

የኖርዌይ ስደተኞች ካውንስል (NCR) ዋና ጸሐፊ ጃን ኢግላንድ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሽልማት መደሰታቸውን በመግለጫ ልከዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአገሪቱ ሰላምን ለማስጠበቅ የሚያደርጉትን ጥረት አጠንክረው እንዲቀጥሉም መልዕክት ልከዋል።

የኖርዌይ ስደተኞች ካውንስል (NCR) ዋና ጸሐፊ ጃን ኢግላንድ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሽልማት መደሰታቸውን በመግለጫ ልከዋል።
የኖርዌይ ስደተኞች ካውንስል (NCR) ዋና ጸሐፊ ጃን ኢግላንድ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሽልማት መደሰታቸውን በመግለጫ ልከዋል።

"ድርጅታችን የኖርዌይ ስደተኞች ካውንስል (NCR) በኢትዮጵያና በኤርትራ ከስደተኞች ጋር ከሚሰሩ ጥቂት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መካከል አንዱ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በሁለቱ ሃገራት መካከ ያመጡትን ለውጥ የዐይን እማኝ ሆነን ለማየት ችለናል። ይህ ለውጥ የመጣው ደግሞ በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረው ግጭትና ቁርሾ ዜጎች ለዓመታ በመፈናቀል ከተሰቃዩ በኋላ ነው” ብለዋል።

ዋና ጸሐፊ ጃን ኢግላንድ አያይዘውም አሁን የኖቤል የሰላም ሽልማት የተቀበሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ የተከሰተውን የብሔር ፍጥጫ ቅድሚያ ሰጥተው በማስተካከል በሕዝቦች መካከል ሰላምን ለማምጣት መሥራት አለባቸው ብለዋል።

“የዛሬው ሽልማት የዶ/ር አብይ አሕመድ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ ነው” ያሉት ጃን ኢግላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሽልማት ያሰጣቸውን በጎ ተግባር አጠናክረው ቀጥለው በሃገሪቱ የተከሰተውን የብሔር ውጥረትን በማርገብ የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ እንደሚያደርጉ ተስፋ እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ በበኩሉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ለሁለት አስርት ዓመታት በኢትዮ ኤርትራ መካከል የነበረውን የድምበር ውዝግብ እልባት በመስጠት ሰላም ማውረድ ችለዋል ሲል አሞግሷቸዋል፡፡

"በዚህም ሽልማቱ ተገቢ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ ከዚህ በኋላ ትልቅ ሥራ ይጠብቃቸዋል፡፡ ይህ ሽልማት በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጋሬጣ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ይበልጥ ሊያበረታታቸው ይገባል፡፡ በአፋጣኝ ሁኔታም በሃገሪቱ ውስጥ እየተፈጠረ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና አለመረጋጋት እንዲሁም የብሄር ግጭቶች እልባት መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡ መንግስታቸው በአገሪቱ ውስጥ ጫና ለመፍጠር እንደመሳሪያ እያገለገለ ያለውን የጸረ-ሽብር ህጉ በድጋሚ ረቆ እንዲያፀድቅ እና ከዚህ በፊት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያደረሱ ተጠርጣሪ አካላት ለሕግ እንዲቀርቡ ማድረግ ይኖርበታል፡፡" ብሏል።

ለዚህ ከፍተኛ የኖቤል ሽልማት 301 እጩዎች ቀርበው ነበር። ዕጩዎቹ 223 ግለሰቦችና 78 ድርጅቶችም ነበሩ።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG