ዋሽንግተን ዲሲ —
በተባበሩት መንግሥታት የትምሕርት፣ የሳይንስ እና ባህል ተቋም በቅርስነት በተመዘገበውና በአሁኑ ሰዓት በሰደድ እሳይ እየጋየ የሚገኘውን የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን ለመታደግ የሄሊኮፕተሮች እርዳታ ከሌሎች አገሮች ተጠይቋል።
ጥያቄውን የተቀበለችው ደቡብ አፍሪካ ስድስት የእሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተሮችን ልትልክ መሆኑንም የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
የ50 ዓመታት ዕድሜ ያለው እና የጎብኝዎች የዐይን ማረፊያ የሆኑ ብርቅዬ የዱር አራዊት እና እጽዋት መናኸሪያ በሆነው በዚህ ስፍራ ከጥቂት ቀናት በፊት የተነሳው የሰደድ እሳት ከ300 ሄክታር በላይ ደን መቃጠሉን መዘገባችን ይታወሳል።
እሳቱ በሙቀትና በንፋስ እየታገዘ በመዛመቱ መጠኑ እየጨመረ መምጣቱን የፓርኩ ሃላፊዎች እየገለጹ ሲሆን ሄሊኮፕተሮቹ በአስቸኳይ ተገኝተው ርብርብ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ አያይዘው እንደተናገሩት እሳቱን ለማጥፋት እየተረባረቡ የሚገኙት የአካባቢው ማኅበረሰብ መሆናቸውን ገልፀው ነገር ግን እየተስፋፋ በመምጣቱ መቆጣጠር እንዳልተቻለ ተናግረዋል።