በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“በእስር ላይ የሚገኙትና የተፈቱት ቁጥራቸው የሚመጣጠን አይደለም” - አቶ በቀለ ገርባ


አራቱ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አባላትና ሌሎች ተከሳሾች
አራቱ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አባላትና ሌሎች ተከሳሾች

ከእስር የተለቀቁት አቶ በቀለ ገርባና አቶ ደጀኔ ጣፋ፤ “በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም በእስር ቤቶቹ ውስጥ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት ቃሉን አክብሮ ሁሉንም ሲፈታ ነው ለውጥ የሚመጣው” ሲሉ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

“በእስር ላይ የሚገኙትና የተፈቱት ቁጥራቸው የሚመጣጠን አይደለም” - አቶ በቀለ ገርባ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:51 0:00

አራቱ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አባላትና ሌሎች ተከሳሾች ክስ እንዲቋረጥ በተወሰነው መሰረት በዛሬው ዕለት፤ አቶ በቀለ ገርባ፤ አቶ ጉርሜሳ አያና፣ አቶ አዲሱ ቡላላ፣ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ አቶ ጌቱ ጋሩማ፣ አቶ ተስፋዬ ሊበን እና አቶ በየነ ሩዳ ከእስር መለቀቃቸው ታውቋል።

የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ከእስር ከወጡ በኋላ በደጋፊዎቻቸው ታጅበው አዳማ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በመሄድ ላይ እያሉ በስልክ አግኝተናቸው ነበር።

ዛሬ ከሰዓት በኋላ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ከእስር የመፈቻ ደብዳቤ ደርሷቸው ከእስር ቤት ግቢ ውስጥ መውጣታቸውን ይናገራሉ።

“በራዲዮና በቴቭዥን እንደተነገረው ሰባት ሆነን ተለቀናል። ማረሚያ ቤቱ መኪና ልናገኝ የምንችልበት ድረስ ሸኝቶናል። ከዛ በኋላ ለቤተሰቦቻችን ስልክ ደወልን። በአሁኑ ሰዓት እጅግ በጣም ብዙ በሚባል ሕዝብ ታጅበን ሌሎቹ ወደ ቡራዮ ወደ ቤታቸው ሄደዋል እኔ ደግሞ ወደ አዳማ እያመራሁ ነው” ብለውናል።

አቶ በቀለ ሕዝቡ ለፍትሕ እያሳየ ያለውን ፍቅር አድንቀው ፤ የኦሮሚያ ፖሊስ አስፈላጊውን ጥበቃ አድርጎ ወደ ቤታቸው እየሸኛቸው መሆኑን ነግረውናል። እጅግ በጣም ብዙ ሕዝብ በየደረሱበት ቦታ እያደረገላቸው ያለው አቀባበልና አሸኛኘት ደግሞ እንዳስገረማቸው ተናግረዋል።

ከመታሰራቸው ከሁለት ዓመት በፊት ያለውን ሁኔታ ሊቀበላቸው አደባባይ ከወጣው ሕዝብ ጋራ ሲያነፃፅሩት ከግምት በላይ አስገራሚ ትዕይንት እንደሆነባቸው ይገልፃሉ።

“ከዚህ በፊትም የተወሰኑ ዓመታት ታሥሬ ወጥቻለሁ። ያኔ በወጣሁ ጊዜ ያጋጠመኝ ነገር .. እንኳን ሰው በቀን መጥቶ ሰላምታ ሊሰጠኝና ደስታውን ሊገልፅልኝ ቀርቶ በምሽት ሰው በማያይይበት ሰዓት አንዳንድ ሰዎች ቤቴ እየመጡ ሰላም ይሉኝና ደስታቸውን ይገልፁልኝ ነበር። የአሁኑ ግን እጅግ በጣም በሚገርም ሁኔታ በጣም ልዩ የሆነ ጥበቃ ተደርጎልኝ ለሌሎቹም እንደዚሁ ተመሳሳይ ነገር ተደርጎላቸው ወደ ቤታችን እየሄድን ነው። በእውነት እኔ ይህንን አንድም ቀን ይሆናል ብዬ የገመትኩት ነገር አይደለም።” ይላሉ።

አቶ በቀለ እርሳቸው ዛሬ ቢለቀቁም ቁጥራቸውን ለመገመት የሚያስቸግር እስረኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ፤ “ምናልባት በሚዲያ አካባቢ የሚታወቁ ጥቂት ሰዎች ስለተፈቱ ሁሉም እስረኛ የተፈታ ይመስላል። በኢትዮጵያ ማረሚያ ቤቶች በተለይም በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አሉ የሚባሉ የፖለቲካ እስረኞች ቁጥራቸው ከተፈቱት ጋራ ቢመዛዘን አሁን የተፈቱት በእውነት እዚህ ግባ የሚባል ቁጥር አይደለም። በጣም ብዙ ሰዎች እስር ቤት ውስጥ አሉ።” ብለዋል።

“ብዛታቸው ብቻ ሳይሆን ለረጅም ዓመታት በየማረሚያ ቤቱ የተሰቃዩ እጅግ በጣም ብዙ ወንድና ሴቶች አሉ፣ ጋዜጠኞች አሉ፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የአየር ኃይል አብራሪዎች፣ ሀገራቸውን ትናንት ከጠላት ሲጠብቁና ሲከላከሉ የነበሩ ሰዎችም ጭምር እስር ቤት ውስጥ አሉ” በማለት የእስረኞቹን ማንነት ይዘረዝራሉ።

ከትምሕርት ገበታ ላይ ተወስደው ከየዩኒቨርስቲው ተሰባስበው ተለቅመው የታሰሩ አሉ። ከሥራ ገበታቸው ላይ ተነስተው ታስረው በየእስር ቤቱ የሚገኙ አሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በተለይ ከጎንደር አካባቢ እጅግ በጣም በርካታ የሆነ ሰው እየታሰረ ይገኛል
የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ

አያይዘውም፤“ከትምሕርት ገበታ ላይ ተወስደው ከየዩኒቨርስቲው ተሰባስበው ተለቅመው የታሰሩ አሉ። ከሥራ ገበታቸው ላይ ተነስተው ታስረው በየእስር ቤቱ የሚገኙ አሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በተለይ ከጎንደር አካባቢ እጅግ በጣም በርካታ የሆነ ሰው እየታሰረ ይገኛል። በፖለቲካ ምክንያት ታስረው ያሉትንና የተፈቱትን ብናይ ቁጥራቸው በጣም የሚመጣጠን አይደለም ነገር ግን እንግዲህ በሁለት ወር ውስጥ ይህን ሁሉ እፈታለሁ ብሎ ቃል ገብቷል በገባው ቃል መሰረት ይፈፅም አይፈፅም እንደሆነ ይህንን አንድ ወር ጠብቀን የመንግሥትን ተአማኒነት እና ተቀባይነት ከምን ደረጃ እንደሆነ የምንገመግምበት ይሆናል።” ብለውናል።

በዛሬው ዕለት ከእስር የተለቀቁት የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ ምክትል ጸሐፊ አቶ ደጀኔ ጣፋም እንደ አቶ በቀለ ገርባ ከእስር ስላልተፈቱት ሰዎች ያላቸውን ስጋት ተናግረዋል።

“የኦሮሞ ልጅም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳለ እስር ቤት ነው ያለው። አሁን እኛ የወጣነው ከ’ፍርጅ ቤት’ (ከቀዝቃዛ ቦታ) ነው።” ይላሉ። በዚህ ቦታ ከነበሩት 13 እስረኞች ውስጥ አራቱ ብቻ መፈታታቸውን ይናገራሉ።

ከኛ መካከል ዘጠኝ ሰው እዛው ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥ መቶ አለቃ ማስረሻ ስጤ፣ መቶ አለቃ አንተነህ ታደሰ፣ ኒሞና ኡርጌሳና ሌሎች በጣም የታመሙ፣ በሽተኞች የሆኑ፣ ተደብድበውና ተሰቅለው ስቃይ ያዩ አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ። ከጎንደር የመጡ የ80 ዓመት አዛውንት ጨለማ ቤት ውስጥ አሉ
የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ ምክትል ጸሐፊ አቶ ደጀኔ ጣፋ

“ከኛ መካከል ዘጠኝ ሰው እዛው ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥ መቶ አለቃ ማስረሻ ስጤ፣ መቶ አለቃ አንተነህ ታደሰ፣ ኒሞና ኡርጌሳና ሌሎች በጣም የታመሙ፣ በሽተኞች የሆኑ፣ ተደብድበውና ተሰቅለው ስቃይ ያዩ አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ። ከጎንደር የመጡ የ80 ዓመት አዛውንት ጨለማ ቤት ውስጥ አሉ” ብለዋል። “የኦሮሞ ሕዝብማ ምኑን ወጣ እኛ ትንሽ የምንታየው የምንፍጨረጨር ነን እንጂ የኦሮሞና የአማራ ሕዝብማ እንዳለ እስር ቤት ውስጥ ነው የሚገኘው” ብለዋል።

አያይዘው፤ “ኢትዮጵያ ትናንትም ዛሬም ነገም የዴሞክራሲ እስር ቤት ነች። ስለዚህ እኛ ሀገራችንን እንደማንኛውም እንዳደጉ ሀገሮች ወደ ዴሞክራሲ አንድ እርምጃ ከፍ እንድትል እንጥራለን። ሁለተኛ ደግሞ በኛ ምክንያት ብዙ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሞቷል። ደሙን አፍስሷል አጥንቱን ከስክሷል ከቤት ንብረቱና ከሀገሩ ተፈናቅሏል። ዛሬም እየሞተ ነው። ስለዚህ ይህንን ሕዝብ ዝም ብለን ማየት የለብንም መንግሥትን አነጋግረን ከዚህ ሕዝብ ጋራ ተወያይ ቁጭ በልና ይህንን ሕዝብ አዳምጥ እንለዋለን። ሁል ጊዜ የኦሮሞን ሕዝብ በኦነግ፣ የአማራን ሕዝብ ደግሞ በግንቦት ሰባት የሚከሰውን የመክሸሻ ጨዋታና ደንባቸውን አቁመው ከሀገር ውስጥም ከውጭም የትም ቦታ እየተሰደበና እየተዋረደ የሚኖረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይችን ሀገር ነፃ አውጥተን ሁላችንም በጋራ የምንኖርባትን ኢትዮጵያ እናደርጋለን ብለን ነው የምንነሳው።” ሲሉ እምነታቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ልጆች ዛሬም ትናንትናም እየተገደሉ ነው። ዛሬም እየተቀበሩ ነው። ስለዚህ ሙሉ ሳይሆን ግማሽ ደስታ ነው። የሚያስደስተን ነገር የሚገደሉት ሲቆሙ ነው እኛ በሕይወት ስለኖረ አግኝተነዋል
የአቶ ደጀኔ ጣፋን ባለቤት ወ/ሮ አሰለፈች ሙላት

የአቶ ደጀኔ ጣፋን ባለቤት ወ/ሮ አሰለፈች ሙላት በበኩላቸው፤ “እንኳን ደስ አለን ለማለት ትንሽ ይከብዳል። የኢትዮጵያ ልጆች ዛሬም ትናንትናም እየተገደሉ ነው። ዛሬም እየተቀበሩ ነው። ስለዚህ ሙሉ ሳይሆን ግማሽ ደስታ ነው። የሚያስደስተን ነገር የሚገደሉት ሲቆሙ ነው እኛ በሕይወት ስለኖረ አግኝተነዋል። ቤተሰብም ሰፈርም ተደስቶ አጅቦት እየተቀበለው ነው። በአንድ በኩል ደግሞ እየተለቀሰ ነው በጣም ያሳዝናል።” ብለዋል።

ገዢው የኢትዮጵያ ፓርቲ ኢሕአዴግ ለ18 ቀናት ካደረገው ግምገማና በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝን ጨምሮ የአራቱ ፓርቲ አመራሮች በጋራ በሰጡት መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከእስር ስለሚለቀቁ ሰዎች ሲናገሩ፤

“በፍርድ ቤት የተፈረደባቸው ወይ ደግሞ በዐቃቤ ሕግ ክስ የተመሰረተባቸው እና ጉዳያቸው እየተጣራ የሚገኙ የፖለቲካ አመራሮችም ሆነ ግለሰቦች በሰሩት ጥፋት መሰረት ይሄ እየተካሄደ እንዳለ የሚታወቅ ነው። ነገር ግን የተሻለ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር እንደዚሁም የዴሞክራሲ ምሕዳራችንን የበለጠ እናሰፋለን ብለን ባልነው መሰረት፣ አንዳንዶቹ ክሳቸውም ተቋርጦ፣የምሕረት ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት ምሕረት ተደርጎላቸው ሕጉና ሕገ መንግሥቱ እና የሕግ አሰራር ሥርዓታችን በሚፈቅደው መሰረት ተጣርቶ የሚወሰዱ እርምጃዎች ይኖራሉ” ማለታቸው ይታወሳል።

አያይዘውም፤ “የሕግ የበላይነት በማይጣስበት ሁኔታና ሕግና ሥርዓቱን ተከትሎም ቢሆን ነገር ግን የዴሞክራሲ ምሕዳራችንና የፖለቲካ ምሕዳራችንን ለማስፋት እንደዚሁም ደግሞ የሚፈጠረው መንፈስ መድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ሥርዓታችንን ሊያጎለብት በሚችልበት ደረጃ የሚስተናገድ ነው የሚሆነው” ብለው ነበር።

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሰሞኑን በሰጠው መረጃ ፤ሰሞኑን ከእስር እየተለቀቁ የሚገኙት እስረኞች የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የይቅርታና የክስ ማቋረጥ እንደሚያደርግ በወሰነው መሰረት የተከናወነ እንደሆነ አስታውቋል።

ከዚህ ውሳኔ በኋላ ታዋቂውን ፖለቲከኛ ዶ/ር መረራን ጨምሮ የተወሰኑ እስረኞች መፈታታቸው የሚታወስ ሲሆን ዛሬ ደግሞ በፖለቲካው መድረክ ጉልህ ስፍራ ያላቸው ፖለቲከኞች ከእስር ተለቀዋል።

በሌላ በኩል በሀገር ውስጥ የእስረኞችን ጉዳይ የሚከታተሉ ተሟጋቾችና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ የኅሊናና የፖለቲካ እስረኞች በኢትዮጵያ መኖራቸውን በመግለፅ ሁሉም እንዲፈቱ ሲወተውቱ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG