Associated Press የዜና አገልግሎት ላይ የወጣ ዘገባ ወደ አውሮፓ የመጓዝ ተስፋ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያን፣ ሶማሊዎችና ሱዳናውያን በመተማ ከተማ እንደሚያልፉ ይገልጻል።
ጽሁፉ በመተማ ድንበር ስለሚደረግ ጥበቃ ሲያወሳ ድንበር ጠባቂዎች ህገ-ወጥ ፈላሽ መስሎ የታያቸውን ሁሉ እያስቆሙ እንደሚጠይቁ ያወሳል። የከተማይቱ የምሽት ክለቦችና ባሮች ከበፊቱ ያነሱ ሰዎች ይገኙባቸዋል። በርግጥ የሸሪዐ ህግ በሚያዘው መሰረት በአገራቸው የአልኮል መጠጥ ከሚከለከልበት ሱዳን የሚመጡት ሰዎች መስህብ መሆናቸው እንዳልቀረ ጽሁፉ ጠቅሷል።
አንድ መቶ ሺህ ህዝብ የሚኖርባት መተማ ከተማ በክልሉ ከኢትዮጵያ፣ ከኤርትራ፣ ከሶማልያና ከሱዳን ወደ አውሮፓ ለመዝልቅ የሚጓዙትን ፈላሾች ለማጓጓዝ ከሚያገለግሉት እፍኝ የማይሞሉ ከተሞች አንዷ ናት።
በአሁኑ ወቅት የመተማ ኑሮ የአይጥና ድመት ጨዋታ ሆኗል። ባለስልጣኖች ከፍተኛ ክትትል እያደረጉ ናቸው። ፈላሾቹ ግን ሞትን እየተጋፈጡ መምጣቱን ቀጥለዋል።
ሰላሳ የሚሆኑ በመተማ በኩል ያለፉ የክርስትና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ከጥቂት ወራት በፊት እስላማዊ መንግስት ነኝ በሚለው ጽንፈኛ ቡድን ከተገደሉ ወዲህ የኢትዮጳይ መንግስት ከፍተኝ ክትትል እያደረገ ነው ይላል ጽሁፉ።
--------
ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ላይ የወጣ ድሁፍ ደግሞ የሰላም ጥበቃ ተልእኮ መሳርያ እንደተሰረቀ ገልጿል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአፍሪቃ ህብረት ሰላም ጥበቃ ተልእኮ መሳርያዎቹ በአከባቢው ግጭት ለመስፋፋት ምክንያት በሆኑት ሃይሎች እጅ እንዲገባ በተደጋጋሚ ፈቅዷል ሲል አንድ ጂኔቫ ያለ የጥናት ቡድን እንደዘገበ ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ላይ የወጣ ጽሁፍ ጠቁሟል።
ባለፉት 10 አመታት ውስጥ ከ 500 በላይ የሚሆኑ ከባድ መሳርያዎችና ሞርታሮች የሚገኙባቸው መሳርያዎች እንደዚሁም ወደ አንድ ሚልዮን ዙር የሚጠጉ ጥይቶች በሱዳንና በደቡብ ሱዳን ካሉት የሰላም ጥበቃ ሃይሎች እንደተሰረቁ ዘገባው ገልጿል።
መሳርያዎቹ እአአ ከ 2005 እስከ 2014 አም በነበረው ጊዜ ውስጥ ከጥብቃ ክፍሎችና ከአቅርቦት ካምዮኖች የተሰረቁት በሃያ ተለያየዩ ጊዚያት እንደሆነ ዘገባው ጠቁሟል።