ወደሞቃዲሾ ከሃርጌሣ ነፍስ አድን እርዳታ ይዞ የገባው የሰብዓዊ ድጋፍ ቡድን ሰሞኑን ያደረሰው በድርቁ ምክንያት ለከፋ ረሃብ ለተጋለጡ ዘጠኝ ሺህ ሶማሊያዊያን ቤተሰቦች መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዜና አውታር አይሪን ዘግቧል፡፡
አንድ የሶሚሊላንድ ቡድን በሞቃዲሾ እንዲህ ዓይነቱን ጉብኝት ሲያደርግ የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ከሶማሊያ መገንጠሏንና ነፃ መንግሥት መመሥረቷን ካወጀች ከ1984 ዓ.ም ወዲህ ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ ማለት ነው የመጀመሪያው ነው፡፡
ስምንት አባላት ያሉበትን ይህንን የሰብዓዊ እርዳታ አድራሽ ቡድን የመሩት የሶማሊላንድ ንግድ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሃሰን አብዲ አወድ "ለዘጠኝ ሺህ ቤተሰቦች ምግብ፣ ለአራት ሆስፒታሎች ደግሞ መድኃኒት እናደርሣለን" ብለዋል፡፡
ቡድኑ እያከፋፈለ ያለው ምግብ ተጠቃሚዎቹን ለአንድ ወር መመገብ የሚችል እንደሆነ ታውቋል፡፡
የሶማሊላንዱ ቡድን በረሃብ እየተጎሣቆሉ ላሉት ሶማሊያዊያን ነፍስ አድን እርዳታ ለማድረስ እየተረባረበ ካለው ዓለምአቀፍ ማኅበረሰብ ጋር ለመቀላቀል እየተዘጋጀ እንደነበረ ይፋ ያደረገው በአውሮፓዊያኑ ነሐሴ ወር መጨረሻ አካባቢ ነበር፡፡
የሶማሊላንዱ ሰብዓዊ እርዳታ ደራሽ ቡድን ቃል አቀባይ ሞሐመድ ሹግሪ ጃማ ዋና ከተማቸው ሃርጌሣ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከሶማሊላንድ ሕዝብና መንግሥት የተለገሠ ወደ ሰባት መቶ ሺህ የአሜሪካ ዶላር (በዛሬ ምንዛሪ ከ12 ሚሊየን በላይ የኢትዮጵያ ብር መሆኑ ነው) መሰብሰባቸውን አስታውቀዋል፡፡
ዕርዳታውን ያደረሱት በሁለት ቡድኖች ተከፋፍለው ሲሆን አንደኛው ወደ ሞቃዲሾ ተጉዞ ምግብ እያከፋፈለ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ዕርዳታውን ይዞ ወደኬንያ ዳዳብ የመጠለያ ሠፈሮች ተጉዟል፡፡
ቡድኑን ሞቃዲሾ ዓለምአቀፍ አይሮፕላን ጣቢያ ተገኝተው የተቀበሉት የመናገሻይቱ ከንቲባ ሞሐመድ አህመድ ኑር ጣርሣን የሶማሊላንዱ ቡድን ዓለምአቀፉን ሰብዓዊ ጥረት መቀላቀሉ ያስደሰታቸው መሆኑን ገልፀው፤ "ለእኛ እርካታን የሚሰጠን የምትሰጡን ልገሣ መጠን ሣይሆን ሃሣባችሁና ከጎናችን መቆማችሁ ነው" በለዋቸዋል፡፡
ሶማሊላንድ በሰሜን ሶማሊያ የምትገኝ ቀድሞ በእንግሊዝ ሞግዚትነት ሥር የነበረች፤ በኋላም በአውሮፓዊያኑ የዘመን አቆጣጠር በ1960 ዓ.ም (የዛሬ ሃምሣ አንድ ዓመት ማለት ነው) መናገሻዋ ሞቃዲሾ የሆነችውን የሶማሊያ ሪፐብሊክ ለመመሥረት የኢጣልያን ሶማሊላንድ የተቀላቀለች ግዛት ነች፡፡
ሶማሊላንድ የዛሬ ሃያ ዓመት ከሞቃዲሾ መገንጠሏንና የራሷን ሪፐብሊክ መመሥረቷን ካወጀች ጀምሮ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በሞቃዲሾ መሩ ግዛት ውስጥ ሁሉ ባልታየ ሁኔታ ሰላማዊ መስተዳድር ፈጥራ ያለች ግዛት ነች፡፡ እነሆ ዛሬ ለክፉ ቀን ደራሽ፣ ሕይወት አዳሽ ድጋፍ ይዛ ለመድረስ በቃች፡፡ የሠላም ዋጋ፤ የመረጋጋት ዋጋ፡፡