በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የተጋነኑ መረጃዎች በሀዋሳና በወላይታ የተከሰቱ ግጭቶችን ማባባሳቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ


በሀዋሳ ከተማ የጨምበላላ በዓል ላይ የተከሰተ ግጭት
በሀዋሳ ከተማ የጨምበላላ በዓል ላይ የተከሰተ ግጭት

በሀዋሳ፣ በወላይታና በወልቂጤ በተፈጠሩ ግጭቶች በሰዎችና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ታወቀ። አካባቢዎቹም ውጥረት እንደነገሰባቸው ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ ገለጹ። ለግጭቶቹ መባባስ ደግሞ የተጋነኑ መረጃዎች አስተዋጾ አላቸው ብለዋል። ከዚህ በላይ ሁኔታዎቹ እንዳይባባሱ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥበትም አሳስበዋል።

የተጋነኑ መረጃዎች በሀዋሳና በወላይታ የተከሰቱ ግጭቶችን ማባባሳቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:13:19 0:00

የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው የከተማዎቹ ነዋሪዎች፤ በሀዋሳ ከተማ የተከበረውን የፊቼ ጨምበላላ የዘመን መለወጫ በዓል ተከትሎ የተነሳው አለመግባባት ወጣቶች ብሔር ለይተው እርስ በእርስ እንዲጋጩ ምክኒያት ሆኗቸዋል ብለዋል።

ይህ ግጭትም ሀዋሳን አልፎ በዛሬ ዕለት ወደ ወላይታ መዛመቱንና በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል። በወላይታ ዞን በሶዶ ከተማ የሚገኙ የተለያዩ ነዋሪዎችን ያነጋገርን ሲሆን ለግጭቱ መነሻ የሆነውን ምክኒያትና ደረሰ የተባለውን አደጋ በተመለከተ ያገኘንው መረጃ የተለያየ ነበር።

በመጨረሻም በከተማው ውስጥ የሰማያዊው ፓርቲ ተወካይ የሆኑትና የዐይን እማኝ ነበረኩ ያሉትን ግለሰብ ስናነጋግር፤ በዛሬው ዕለት ሰዎች መጎዳታቸውንና ከፍተኛ የመንግሥትና የግለሰቦች ንብረት መውደሙን ተናገረዋል።

በከተማዎቹ የሚነገረውና የሚሰራጨው መረጃ ከደረሰው አደጋ በላይ የተጋነነ በመሆኑ ለተጨማሪ ግጭቶችና “የእኔ ብሔር እዛ እየተጠቃ፤ እኔ ለምን ዝም አላለሁ?” በሚል ለሌላ ፀብና ጥፋት እንዲጋበዙ አድርገዋል ብለዋል።

በግጭቶቹ ውስጥ እየተሳተፉ የሚገኙት ወጣቶችም በሰፈር ጎራ ከፍለው በድንጋይና እጃቸው ላይ ባሉ መሳሪያዎች እርስ በእርስ ይጠቃቃሉ ብለውናል።

በሀዋሳ ከተማም በተምሳሳይ እንዲሁ በተለምዶ ፤ ሞቢል ሰፈር ፣ አላሙራና አዲሱ ገቢያ በሚባሉ አካባቢ ሁለት የተለያዩ ፅንፍ ተያዞ አንዱ የአንዱን ንብረት ማቃጠልና መዝረፍ እንዳለ ነዋሪዎቹ ገልፀውልናል። በዚህ መካከል ማኅበረሰቡ በጭንቀት ውስጥ መውደቁንና የቻለ ልጆቹን ይዞ ሰላም ነው ወዳለው አካባቢ እየሄደ እንደሆነ ሌላው ደግሞ በሩን ዘግቶ እንደተቀመጠ ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።

እርስ በእርስ በሚደረግ የስልክ ልውውጥም “ይህን ያህል ሰው እዚህ ቦታ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደለ” የሚሉ መረጃዎች እንደሚነገሩ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በግጭቱ የሰው ሕይወት ማለፉን እንጂ እስካሁን ስንት ሰው እንደሞተ ለማጣራት ባደረግነው ሙከራ መረጃ ማግኘት አልቻልም።

በተጨማሪም የሰዎች አካል መጎዳቱን እንጂ ምን ያህል ሰው እንደተጎዳ መረጃ ማግኘት አልቻልም።

በጉዳዩ ላይ የደቡብ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፈ አቶ ሰለሞን ኃይሉን ለማነጋገር ከፍተኛ ጥረት አድርገን የነበረ ቢሆንም ስልካቸው ስለማይነሳ ልናገኛቸው አልቻልንም።

በሌላ በኩል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ ለክልሉ ቴሌቭዥን በሰጡት መግለጫ የክልልሉ መንግሥት ግጭቱን የማረጋጋት ሥራ እሠራ ነው ብለዋል።

በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምሕር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል ኃይሉ ከግጭቱ ጀርባ ብዙ ችግሮች ስላሉ የፌደራል መንግሥት በተለይም ደግሞ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ ጣልቃ ገብተው ዘላቂ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን በተመለከተ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በሰጠው የጹሑፍ መግለጫ፤ መንግሥት የተከማመሩ የሕዝብ ችግሮችን ለመፍታት በመሥራት ላይ ባለበት በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ጊዜያዊ ግጭቶች መከሰቱን ጠቅሶ፤ “አካባቢያዊ ወሰንና ሌሎች መሰል ምክንያቶችን መነሻ በማድረግ ለዘመናት አብሮ በኖረው ሕዝቦች መካከል ጥርጣሬን የሚፈጥሩ እና ለግጭት የሚያነሳሱ ሴራዎች ተስተውለዋል።” ብሏል።

ያነጋግረናቸው ነዋሪዎች፣ የሕግ ባለሞያውም ሆነ መንግሥት በሰጡትና በሚናገሩት መገልጫ የሀገሪቱን ሰላም ለማደናቀፍ የሚሰሩ አካላት አሉ ቢሉም “እነዛ አካላት እነ ማን ናቸው?” - የሚለውን ለማጣራት ባደረግነው ጥረት በመንግሥት በኩል ከፌደራልም ሆነ ከክልል ባለሥልጣናት ለደወልናቸው ስልኮች ምላሽ የሚሰጠን ልናገኝ አልቻልንም ።

የሀዋሳ ዩኒቨርስቲው ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ዳንኤል ከፍተኛው ሥራ ያለው መንግሥት ጋራ ቢሆንም ሕብረተሰቡ እስከዛሬ አብሮት የቆየው አብሮ የመኖር ማኅበራዊ እሴቱ እንዳይበላሽ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ሲሉ መክረዋል።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG