ኤጀንሲው በ1969 እኤአ በራሱ ስቱዲዮ መርሐ-ግብሮችን እያዘጋጀ ማሰራጨት መጀመሩንም «ኢትዮጵያ፣ ትምህርታዊ ራዲዮ እና ቴሌቭዥን» የተሰኘው የቶማስ ዲ ቲልሰን እና ደምሰው በቀለ ቆየት ያለ ጥናት ይጠቁማል።
በዓመታት ውስጥ በተለያየ አቀራረብ ፣ሲፈካ ሰፈዝ የባጀው ትምህርትን በቴሌዥን የማዳረስ አሰራር ከሰሞኑ ወደ ሌላ ምዕራፍ የተሻገር ይመስላል።ኢትዮጵያ 9 አዳዲስ የትምህርት ቴሌቭዥን ጣቢያዎችን በያዝነው ሳምንት ከፍታለች።
የአሁኑ እርምጃ የሰመረው የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር፣የህጻናት አድን ድርጅት፣ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት ድርጅት እና SES የተሰኘው ዓለም አቀፍ የሳተላይት አውድማ አቅራቢ እና ስርጭት አሳላጭ ድርጅት ባደረጉት ትብብር ነው።
በስምንት የተለያዩ ቋንቋዎች በክልሎች እና በፌዴራሉ መስሪያ ቤት ጥላ ስር ስራቸውን የሚከውኑት ጣቢያዎች ፣በሚሊየን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከሰሞነኛው የኮቪድ 19 ስጋት ተጠብቀው ዕውቀት ይገበዩ ዘንድ እንደሚያገለግሉ ተስፋ ተጥሎባቸዋል። ግልጋሎታቸው ከሰሞነኛ መፍትሄነት ተሻግሮ ለዓመታት የሚዘልቅ ርባና እንደሚኖረውም የአሜሪካ ድምጽ ያናገራቸው የተቋማቱ ተወካዮች ያወሳሉ።
የሀብታሙ ስዩምን ሙሉ ዘገባ ያዳምጡ።