ተመድ በምዕራብ ጎንደር ዞን የሱዳን ፍልሰተኞች ወቅታዊ ሁኔታ እንደሚያሳስበው አስታወቀ

  • ቪኦኤ ዜና

በዐማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን አውላላ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ሱዳናውያን ፍልሰተኞች የገጠማቸው ችግር እንዳሳሰበው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በድጋሚ አስታውቋል።

ፍልሰተኞቹ፣ አውላላ ከተሰኘው የተባበሩት መንግሥታት ጣቢያ ለቀው በመውጣት በመንገድ ዳር እየኖሩ ያሉት፣ በተደጋጋሚ በታጣቂዎች የሚደርስባቸውን ጥቃት በመሸሽ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡

አንድ ሺሕ የሚደርሱ የሱዳን ፍልሰተኞች፣ በዐማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን የሚገኘውን አውላላ የተባለ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መጠለያ ጣቢያ ለቀው በመውጣት በአውራ ጎዳና ላይ መኖር ከጀመሩ፣ አንድ ወር ተቆጥሯል።

በትጥቅ የታገዘ ዘረፋ እና እገታ እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ፣ እንዲሁም በመጠለያ ጣቢያው ተኩስ እየተከፈተባቸው እንደኾነ የሚገልጹት ፍልሰተኞቹ፣ ደኅንነት እንደማይሰማቸው በመግለጽ ከመጠለያ ጣቢያው ርቀው መሸሻቸውን ያስረዳሉ፡፡

SEE ALSO: በሰሜን ኢትዮጵያ የሱዳን እና የኤርትራ ፍልሰተኞች መጠለያቸውን ለቀው ወጡ

ትላንት በጉዳዩ ላይ መግለጫ ያወጣውና፣ የረኀብ አድማ ላይ ያሉ ፍልሰተኞች መኖራቸውን የገለጸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር /ዩኤንኤችሲአር/፣ ኹኔታቸው እንደሚያሳስበው በድጋሚ አስታውቋል።

የፍልሰተኞቹን የደኅንነት ስጋት እንደሚረዳ ኮሚሽኑ ገልጾ፣ በመንገድ ዳር ኾነው ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው፣ በአደገኛ የንጽሕና ኹኔታ ውስጥ መኖራቸውና አንዳንዶቹም የረኀብ አድማ መጀመራቸው፣ የደኅንነታቸውን ኹኔታ ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል፤ ብሏል፡፡

ከሱዳን ደንበር 70 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ወደሚገኙት አውላላ እና ኩመር የተባሉ የተመድ መጠለያ ጣቢያዎች የገቡት ፍልሰተኞቹ፣ በሁለቱ የሱዳን ተፋላሚ ጄኔራሎች መካከል በቀጠለው ጦርነት ወደ ኢትዮጵያ ለመሻገር የተገደዱ ናቸው።

አንድ የርዳታ ሠራተኛ ባለፈው ሳምንት ዐርብ መገደሉን ያስታወቀው ኮሚሽኑ፣ በአማራ ክልል በመከላከያ ኀይል እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከቀጠለው ግጭት ጋራ በተያያዘ ያለው የጸጥታ ኹኔታ ለሠራተኞቹም ጭምር እንደሚያሰጋው አመልክቷል።

በአሜሪካ ኦሪገን ግዛት መሠረቱን ያደረገ ትርፋማ ያልኾነ የሕክምና ቡድን ሹፌር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲያሽከርከር በነበረው መኪና ላይ በተከፈተው ተኩስ ሕይወቱ ማለፉን፣ ድርጅቱ በያዝነው ሳምንት አረጋግጧል።

በሰሜን ጎንደር ዞን ከሚገኙት የኩመር እና አውላላ መጠለያ ጣቢያዎች፣ ከአንድ ሺሕ በላይ የሱዳን ስደተኞች ለቀው መውጣታቸው፣ አንድ ሰው መገደሉን በመጠለያ ጣቢያው ተጠልለው የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች፣ ጠቅሰን ከቀናት በፊት መዘገባችን ይታወሳል።

SEE ALSO: ከሱዳን እየሸሹ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ ነው

ኮሚሽኑ በአውላላ መጠለያ ጣቢያ የውኃ፣ የጤና እና ሌሎችም አገልግሎቶች እንደሚገኙ ኮሚሽኑ አስታውቆ፣ ፍልሰተኞቹ ወደ መጠለያው እንዲመለሱ ጠይቋል።

የኩመር መጠለያ ጣቢያ፣ ከሱዳን፣ ከኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን የመጡ ስድስት ሺሕ የሚደርሱ ፍልሰተኞችን ሲያስተናግድ፣ የአውላላ መጠለያ ደግሞ ሁለት ሺሕ የሚኾኑና በአብዛኛው ከሱዳን እና ደቡብ ሱዳን የመጡ ፍልሰተኞችን እንደያዘ ታውቋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት፣ 1ነጥብ8 ሚሊዮን ፍልሰተኞችን በማስተናገድ ላይ ስትኾን፣ በአፍሪካ ብዛት ያላቸው ፍልሰተኞችን በማስተናገድ ከዑጋንዳ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡