ዩክሬን ሩሲያ፣ ዩናይትድ ስቴትስና የተባበሩት መንግሥታት

Your browser doesn’t support HTML5

ዩክሬን ሩሲያ፣ ዩናይትድ ስቴትስና የተባበሩት መንግሥታት

ሩሲያ በዩክሬን ድንበር ባከመቸችው ጦር ጥቃት ልትሰንዝር ትችላለች የሚለውን የዩናይትድ ስቴትስ ማስጠንቀቂያ ተከትሎ 10 የሚደርሱ አየር መንገዶች በረራዎቻቸውን አቋርጠዋል፡፡ ዩክሬን ግን ትላንት ሰኞ ባወጣችው መግለጫ ወደ ምስራቅ አውሮፓ ለሚደረጉ በረራዎች የአየር መስመሩ ክፍትና ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን አስታውቃለች፡፡ በሌላም በኩል የሩሲያው ፕሬዚዳንት አገራቸው ከዩክሬን ይገነጠላሉ ለተባሉ ሁለት ግዛቶች፣ ነጻ ስለመሆናቸው እውቅና እንደምትሰጥ አስታውቀዋል፡፡ ይህንም ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ትላንት ሰኞ ምሽቱን አስቸኳይ ስብሰባ አድርጓል፡፡

የጀርመኑ ሉፍታንዛ ወደ ዩክሬን የሚያደርገውን በረራ ከትላንት ሰኞ ጀምሮ ያቋረጠ መሆኑን በመግለጽ በረራውን ካቋረጠው ከኔዜርላንዱ ኬ.ኤል.ኤም (KLM) አየር መንገድ ጋር ተቀላቅሏል፡፡

የአገሪቱ ሉፍታንዛ አየር መንገድ ወደ ዩክሬንም ሆነ ከዩክሬን የሚያደርገውን በረራ ከመሰረዙ በፊት ባለፈው እሁድ ከኬየቭ ከተማ የመጡ መንገደንኞች ከጀርመኒቷ ፍራንክፈርት ከተማ አርፈዋል፡፡

የአውሮፓን የተወሰነ ክፍል ጨምሮ፣ የስዊዝ፣ የብራስልስና ኦስትሪያ አየር መንገዶችን በባለቤትነት የያዘውና የጀርመኑን አርማ ያነገበው ሉፍታንዛ አንዳንዶቹ አገሮች ኤምባሲዎቻቸውን ወዳዛወሩበት ወደ ምዕራባዊ ዩክሬን፣ ለቪቭ መብረሩን ይቀጥላል፡፡

ከዚህ በቀር ሌሎቹ የስካንድኔቪያን አየር መንገዶችና የፈረንሳይ አየር መንገድ ከፓሪስ ኪየቭ የሚደረገውን በረራ ከዛሬ ማክሰኞ ጀምሮ አቁመዋል፡፡

የዩክሬን መሠረተ ልማት ሚኒስትር ኦሌክሳንደር ኩብራኮቭ “መንግሥት የተቋረጡ አየር መንገድ በረራዎችን መተካት በሚችልባቸው መንገዶች ዙሪያ እየሰራ መሆኑን” አስታውቀዋል፡፡

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ከምስራቅ ዩክሬን ለሚገነጠሉት ክልሎች እውቅና የሰጡበትን ሰነድ ሲፈርሙ

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሩሲያው ፕሬዚዳንት አገራቸው ከዩክሬን የሚገነጠሉ ሁለት ግዛቶች ነጻ ስለመሆናቸው እውቅና እንደምትሰጥ ካስታወቁ በኋላ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ትላንት ሰኞ ምሽቱን አስቸኳይ ስብሰባ አድርጓል፡፡

በተባበሩት መንግስታት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶመስ ግሪንፊልድ፣ ለጸጥታው ምክር ቤት እንደተናገሩት የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑትን በምስራቅ ዩክሬን ለሚገኙ ዶኔትስክ እና ሉሃንስክን እንደ ነጻ ግዛቶች በመቁጠር እውቅና መስጠታቸው ምንም ባላደረገችው ዩክሬን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው ብለዋል፡፡

አምባሳደር ሊንዳ ቶመስ ግሪንፊልድ፣ እንዲህ ብለዋል

“ፕሬዚዳንት ፑትን ወታደሮቻቸውን በዚህ ክልል እንደሚያሰፍሩ ካስታወቁ በኋላ ሰላም አስከባሪዎች ብለው ሰይመዋቸዋል፡፡ ይህ ከንቱ ነገር ነው፡፡ በትክክል ምን እንደሆኑ እናውቃለን፡፡ እሳቸው በመላው ዓለም ፊት ይህን ማድረግ መርጠዋል፡፡ ይህን ትኩረት ሰጥተነው ልምንመለከተው ይገባል እንጂ ችላ ልንለው አያስፈልግም፡፡ ታሪክ እንደሚያስተምረን እንዲህ ያሉ ጠበኝነትን ችላ ማለት የበለጠ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ ሩሲያ ያለምንም ምክንያት በዩክሬንን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ላይ በግልጽ ጥቃት ሰንዝራለች፡፡ ይህ የተባበሩት መንግሥታት አባል በሆነቸው ዩክሬን ላይ የተፈጸመ ጥቃት ነው፡፡ የዓለም አቀፉን ህግና መርህ የሚጥስና ቻርተራችንን የሚጋፋ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ያሁኑ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ፑቲን እርምጃ፣ ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወረራ ለመፈጸም ተጨማሪ ምክንያት ለመፍጠር የምታደርገው ጥረት ማሳያ ነው፡፡”

በተባበሩት መንግስታት የሩሲያው አምባሳደር “ዩናትይትድ ስቴትስና ምዕራባዊ አጋሮችዋ ዩክሬንን ወደ ጦር ግጭት ጠብ አጫሪነት እየገፏፏት ነው” ሲሉ ከሰዋል፡፡

ትናንት ማታ በተደረገው የአስቸኳይ የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የተናገሩት የሩሲያው ቋሚ መልዕክተኛ ቫሲሊ ኔበኔዚያ ፕሬዚዳንት ፑትን ዶኔትስክ እና ሉሃንስክን እንደ ነጻ ግዛት የሚያውቋቸው መሆኑን ማወጃቸውና በሁለቱ አገሮች መካከል የሩሲያን ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን እንደሚያሰፍሩ መግለጻቸውን ተናግረዋል፡፡

በመንግሥታቱ ድርጅት የዩክሬን ቋሚ መልዕከተኛ የሆኑን ሰርጌይ ኪየስ ላያታስያ የፕሬዚዳንቱን ንግግር አስመልክቶ የሚከተለውን ተናግረዋል፡፡

“በቻርተሩ አንቀጽ 51 መሠረት ዩክሬን በግሏም ሆነ በቡድን ራሷን የመከላከል ተፈጥሯዊ መብት አላት፡፡ እኛም ለሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገዱን መርጠናል እሱንም አጠንክረን እንደያዝን እንቆያለን፡፡ እኛ በመሬታችን ላይ ነን፡፡ እኛ ምንም ሆነ ማንንም አንፈራም፡፡ ለማንም የምንከፍለው እዳ የለብንም፡፡ ለማንም አሳልፈን የምንሰጠው ምንም ነገር የለም፡፡ ምንም ይሁን ምን ግን ይህ የካቲት 2014 ሳይሆን የካቲት 2022 መሆኑ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ ሊኖር አይገባም፡፡”

ሩሲያ በርግጥ የዛሬ ስምንት ዓመት ባደረገችው ወረራ የክሬሚያን ሰርጥ ከዩክሬን ነጥቃለች፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአውሮፓ ህብረትና እንግሊዝ፣ ሞስኮ የወሰደችውን አቋም ተከትሎ፣ “የዓለም አቀፉን ህግና ደንብ የሚጥስና ዩክሬንን ሉዐላዊነት የሚጋፋ ነው” በሚል የመጀመሪያውን ዙር ማዕቀብ መጣላቸውን አሳውቀዋል፡፡

አገሮቹ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባም ላይ ለዩክሬን ሉዓላዊነት መከበር እንደሚቆሙ ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል፡፡