የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ከቻይናው ፕሬዝደንት ሺ ጂንፒንግ ጋራ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ተገናኝተው መነጋገር እንደሚሹ ቻይናን በመጎብኘት ላይ ያሉት የዋይት ሃውስ ከፍተኛ አማካሪ ለሺ ጂንፒንግ ገልጸውላቸዋል።
ከእ.አ.አ 2016 ወዲህ ቻይናን የጎበኙ የመጀመሪያው የዋይት ሃውስ ብሔራዊ የፀጥታ አማካሪ የሆኑት ጄክ ሰለቨን ለሶስት ቀናት በሃገሪቱ ያደረጉትን ጉብኝት ባጠናቀቁበት በዛሬው ዕለት ነበር ፕሬዝደንት ባይደን ከሺን ጂንፒንግ ጋራ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ለመነጋገር እንደሚሹ ያስታወቁት።
ሰለቨን በቻይና ቆይታቸው ከሃገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ዋንግ ዪ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋራ ተወያይተዋል።
የሰለቨን ጉብኝት የመጣው ቻይና የአሜሪካ አጋር ከሆኑት ጃፓን እና ፊሊፒንስ ጋራ ከፍተና ውጥረት ውስጥ ባለችበት ወቅት ነው።
በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለው ፉክክር ወደ ግጭትና መፋጠጥ እንዳያመራ ለመሥራትና በጋራ ፍላጎቶቻቸው ላይ ግን በጋራ ለምሥራት ባይደን እንደሚሹ ሰለቨን ለሺ ጂንፒንግ ገልፀውላቸዋል።
ሺ በበኩላቸው “ከፍተኛ ለውጦች” የሚታዩበት ወቅት ቢሆንም፣ ቻይናና አሜሪካ መልካም ግንኙነታቸውን መጠበቅ እንደሚችሉ ለሰለቨን አስታውቀዋል።