የደቡብ ሱዳን መንግሥት ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የቆየውንና የመጀመሪያዎቹ አባላቱ ዛሬ ጁባ የሚገቡትን የአማጽያኑን ቀዳሚ ቡድን ለመቀበል በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታወቀ ።
ዋሽንግተን ዲሲ —
የቀድሞ ምክትል ፕሬዚደንት ሪያክ ማቻር ታማኞቹ አማጽያን እንዳሉት በዋናው ተደራዳሪ ታባን ዴንግ ጋይ የሚመራው ቀዳሚ ቡድን ፓካግ ከሚባለው አካባቢ ተነስቶ ኢትዮጳያ ጋምቤላ በኩል አድርጎ ጁባ ይገባል።
መንግስታችን አማጽያኑን የሚቀበል ከፍተኛ ኮሚቴ አቁዋቁሙዋል ሲሉ የደቡብ ሱዳን የማስታወቂያ ሚኒስትር ማኢክል ማኩኤይ ገልጸዋል። የአማጽያኑ ወደ ጁባ ጉዞ በከፊልም በሎጂስቲክስ ችግር ገጥሞት ቆይቱዋል።
የአማጽያኑ ቀዳሚ ከመንግሥቱ ወገን አቻዎቹ ጋር ሆኖ የሰላም ውሉ አተገባባር ላይ በጋራ እንዲሰራ ይጠበቅበታል።
የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ማኩዌይ “የአማጽያኑ ቀዳሚ ቡድን በመምጣቱ መንግሥታችን ደስ ብሎታል" ብለዋል።
"የደቡብ ሱዳን መንግሥት በደስታ ይቀበላቸዋል። ምክንያቱም ስምምነቱን በተግባር የመተርጎም እንቅስቃሲውን ለመጀመር ያስችላልና። ሂደቱ ከተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ በጣም ዘግይቱዋል። ስለዚህ ቀዳሚው ቡድን በመምጣቱ ስራውን ለመጀመር ይቻላል አነሱ በሌሉበት ሌሎቹ ወገኖች ስራውን ሊቀጥሉ አይችሉም እና" በማለትም ሃሳባቸውን ገልጸዋል።
በሰላም ስምምነቱ የተመሰረቱት ተቁዋማት ሙሉ በሙሉ ስራቸውን ማከናወን ይችላሉ ሲሉ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።