በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ተጠርጣሪው ፍ/ቤት ቀረበ

  • ቪኦኤ ዜና
በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ተጠርጣሪው የቀድሞው የፖሊስ አባል ፉልጌንሴ ካይሼማ ፍ/ቤት ቀረበ

በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ተጠርጣሪው የቀድሞው የፖሊስ አባል ፉልጌንሴ ካይሼማ ፍ/ቤት ቀረበ

እ.አ.አ በ1994 በሩዋንዳ በተፈጸመው የዘር ማጥፋት እልቂት፣ ከጥቃት ለማምለጥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተሸሸጉ ኹለት ሺሕ ቱትሲዎች እንዲገደሉ ትዕዛዝ አስተላልፏል፤ በሚል የተጠረጠረውና ባለፈው ረቡዕ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተያዘው ግለሰብ፣ ዛሬ ኬፕ ታውን ውስጥ በሚገኝ ፍርድ ቤት ቀርቧል።

የቀድሞው የፖሊስ አባል ፉልጌንሴ ካይሼማ፣ አምስት ክሦች ሲቀርቡበት፣ ከእነርሱም ኹለቱ፣ በዚያች አገር የጥገኝነት ጥያቄውን በሚያቀርብበት ወቅት አጭበርብሯል፤ የሚሉ ክሦች ናቸው።

ካይሼማ፣ የሩዋንዳ ዜግነቱን በመደበቅ ብሩንዲያዊ እንደኾነ አስመስሎ መዋሸቱ እና የሐሰት ስም መጠቀሙ፣ በክሡ ላይ ተመልክቷል።

SEE ALSO: በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ተጠርጣሪው በደቡብ አፍሪካ ተያዘ

በዛሬው የኬፕ ታውኑ የፍ/ቤት ውሎ፣ ተጠርጣሪው ግለሰብ፣ የእምነት ክሕደት ቃል እንዲሰጥ አለመጠየቁ ታውቋል፤ ችሎቱም ለግንቦት 25 ቀን ተቀጥሯል።

የቀድሞው የፖሊስ አባል፣ ፉልጌንሴ ካይሼማ፣ በይፋ ክሥ ከተመሠረተበት ጀምሮ፣ ላለፉት 22 ዓመታት በሽሽት ላይ ነበር። ከኬፕታውን 59 ኪ.ሜ. ላይ በሚገኝ በአንድ የወይን እርሻ ላይ፣ ረቡዕ ዕለት መያዙ ታውቋል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ካይሼማ ያለበትን ለሚጠቁም፣ የአምስት ሚሊዮን ዶላር ጉርሻ እንደሚሰጥ አስታውቆ ነበር።

ሌላው የዘር ማጥፋት ጠንሳሽ የተባለው ፌሊሲን ካቡጋ፣ ከ26 ዓመታት ሽሽት በኋላ፣ ከሦስት ዓመት በፊት፣ በፈረንሳይ ውስጥ መያዙ ይታወቃል።

እ.አ.አ በ1994፣ በሩዋንዳ፥ በአክራሪ ሁቱዎች በተፈጸመ የዘር ማጥፋት፣ 800ሺሕ የሚኾኑ ቱትሲዎች መገደላቸው ይታወሳል።