ሶማሊያ፣ በሞቃዲሾ የሚገኙት የኢትዮጵያ አምባሳደር ከሀገር ለቀው እንዲወጡ ማዘዟን፣ የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ዛሬ ኀሙስ፣ መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ በመግለጫው፣ “የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር መሐመድ ዋሬ፣ ከዛሬ ኀሙስ ጀምሮ በ72 ሰዓታት ውስጥ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸውን” አመልክቷል፡፡
በተጨማሪም፣ ከፊል የራስ ገዝ ግዛት በኾነችው ፑንትላንድ እና ራሷን እንደ አገር በምትቆጥረው በተገንጣይዋ የሶማሊላንድ ግዛት ውስጥ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች እንዲዘጉ ወስና ቀነ ማስቀመጧን ሶማሊያ ይፋ አድርጋለች።
በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዛ ባሬ የተመራው የዛሬው የካቢኔ ስብሰባ ውሳኔውንና ትእዛዙን ያስተላለፈው፣ በፑንትላንድ የገንዘብ ሚኒስትር መሐመድ ፋራህ የተመራ የሚኒስትሮች ልኡካን ቡድን፣ ትላንት ረቡዕ፣ መጋቢት 25 ቀን በአዲስ አበባ ተገኝቶ ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደ’ኤታ ምስጋኑ አረጋ ጋራ የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጉን ተከትሎ ነው፡፡
የፑንትላንድ የሚኒስትሮች ልዑካን ቡድን በአዲስ አበባ ጉብኝት ያደረገው፣ የራስ ገዝ አስተዳደሯ መንግሥት፣ በሶማሊያ ሕገ መንግሥት ላይ የተደረገውን ማሻሻያ በመቃወም ለፌዴራሉ መንግሥት እውቅና እንደማይሰጥ ካሳወቀ በኋላ ነው፡፡
“ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያው የተደረገው፣ የሶማሌ ሕዝብ እውቅና ሳይኖር ነው፤” ያለው የፑንትላንድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ በጉዳዩ ላይ ሕዝበ ውሳኔ እስኪደረግ ድረስ፣ ለሞቃዲሾው መንግሥት ዕውቅና በመንፈግ “ፑንትላንድ የራሷ የኾነ ሁሉን አቀፍ መንግሥት ይኖራታል፤” ሲል፣ ባለፈው ሳምንት እሑድ መጋቢት 22 ቀን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ መግለጫው በወጣ በሦስተኛው ቀን ነው፣ የፑንትላንድ የሚኒስትሮች ልዑክ በአዲስ አበባ ጉብኝት ያካሔደው፡፡
በጉዳዩ ላይ፣ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሰጠው መግለጫ፣ “የኢትዮጵያ መንግሥት በሶማሊያ የውስጥ ጉዳይ ላይ እየፈጸመ ያለው ግልጽ ጣልቃ ገብነት፣ የሶማሊያን ነጻነት እና ሉዓላዊነት የሚጥስ ነው፤” በማለት ወንጅሏል።
የሶማሊያ የማስታወቂያ ሚኒስትር ዳውድ አዌይስ ጃማ፣ ከአሜሪካ ድምፅ የሶማሊኛ አገልግሎት ጋራ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ የፑንትላንድ ባለሥልጣናትን የኢትዮጵያ ጉብኝት ተከትሎ የሶማሊያ መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ ምክንያት፣ “ኢትዮጵያ በሶማሊያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቷን መቀጠሏ ነው፤” ሲሉ አስረድተዋል።
“በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት በተደጋጋሚ እየጣሰች ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት፣ ሁለት የኢትዮጵያ ቆንስላዎችን በመዝጋት በሞቃዲሾ የሚገኙትን የኢትዮጵያ አምባሳደር እና የዲፕሎማቲክ ሠራተኞቻቸውን ወደ አገራቸው ለመላክ ውሳኔ አስተላልፏል፤” በማለትም አክለው አብራርተዋል።
SEE ALSO: ሶማሊያ የኢትዮጵያን አምባሳደር ከሃገሯ አስወጣች“የቆንስላው ጉዳይ ሶማሊያን አይመለከታትም፤” ያሉት ሶማሊላንድ እና ፑንትላንድ በበኩላቸው፣ ውሳኔውንና ትእዛዙን “ተራ ሕልም” ሲሉ አጣጥለዋል፡፡
የፑንትላንድ የማስታወቂያ ሚኒስትር መሐሙድ አይዲድ ድሪር፣ የዛሬውን የመንግሥት ውሳኔ አስመልክቶ ለቪኦኤ የሶማሊኛ አገልግሎት በሰጡት ምላሽ፣ “ሞቃዲሾ በማያስተዳድረው ግዛት ላይ ቁጥጥር ለማድረግ እየሞከረ ነው፤” ሲሉ ከሰዋል።
“አሸባሪዎችን ማጥፋትና በመላ አገሪቱ አስተዳደሩን ማስፈን የተሳነው ሞቃዲሾ፣ አሁን ደግሞ በማያስተዳድረው ሰላማዊ ክልል ላይ ውሳኔውን ለመጫን እየሞከረ ነው፤” ያሉት የማስታወቂያ ሚኒስትሩ፣ በፑንትላንድ የሚገኘውን ቆንስላ ሊዘጋ እንደማይችል ገልጸዋል፡፡
የሶማሊላንድ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሮዳ ጃማ ኤልሚም እንዲሁ፣ ከቪኦኤ ሶማሊኛ አገልግሎት ጋራ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የሞቃዲሾን ውሳኔ “ሕልም ብቻ” ሲሉ አጣጥለዋል።
አክለውም “የሞቃዲሾ መንግሥት በሶማሊላንድ የኢትዮጵያ ቆንስላ ከመከፈቱ ጋራ በተገናኘ የሚመለከተው ነገር የለም፡፡ በመኾኑም ውሳኔው ከእኛ ጋራ ምንም ግንኙነት የለውም። በሶማሊላንድ ላይ ምንም ዐይነት ተጽእኖ አይኖረውም፤” ብለዋል፡፡
ሞቃዲሾ የኢትዮጵያን አምባሳደር የማስወጣቷና ቆንስላዎችን የመዝጋቷ ዘገባ ከመውጣቱ አስቀድሞ፣ ዛሬ ረፋድ ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት፣ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብዩ ተድላ፣ የፑንትላንድ ባለሥልጣናት ጉብኝት ከሰሞነኛ ጉዳዮች ጋራ እንደማይገናኝ ተናግረዋል፡፡
ከፑንትላንድ ባለሥልጣናት ጋራ ስለተደረገው ውይይትም ያብራሩት ቃል አቀባዩ፣ የራስ ገዟ ባለሥልጣናት ጉብኝት፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ያላቸውን ግንኙነት ታሳቢ ያደረገ አይደለም፤ ብለዋል፡፡
ስለ ጉዳዩ የአሜሪካ ድምፅ ተጨማሪ ማብራሪያ የጠየቃቸው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብዩ ተድላ፣ በማኅበራዊ የብዙኀን መገናኛዎች ከተሰራጨው መረጃ ውጭ የኢትዮጵያ መንግሥት በይፋ ስለ ጉዳዩ የተናገረው አለመኖሩን አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከፑንትላንድ ጋራ ያላት ግንኙነት አዲስ እንዳልኾነ ብትገልጽም፣ “የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ የፌዴራል መንግሥቱ ኃላፊነት ነው፡፡ አንድ አገር ከሌላ አገር ግዛት ጋራ የሚፈራረመው ስምምነት የሶማሊያን ሉዓላዊነት የሚፃረር ነው፤” ሲሉ፣ የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር አዌይስ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ከፍተኛ የአለመግባባት እና የውጥረት ምንጭ የኾነው፣ የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ የወደብ መዳረሻ ስምምነት፣ ሶማሊያ ለወሰደችው ርምጃ መንሥኤ መኾኑን፣ ሮይተርስ ሁለት የሶማሊያ ባለሥልጣናትን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡
የባሕር በር የሌላት ኢትዮጵያ፣ ባለፈው ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ 20 ኪ.ሜ. የሚረዝም የባሕር ጠረፍ ከሶማሊላንድ በኪራይ ለማግኘትና በምትኩ ለሶማሊላንድ እውቅና ለመስጠትና ከአየር መንገድ መጠኑ ያልተገለጸ ድርሻ ለማካፈል የመግባቢያ ሰነድ መፈረሟ ይታወቃል፡፡
በስምምነቱ ምክንያት፣ “ሉዓላዊነቴ ተጥሷል” በምትለው ሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል፣ ውጥረቶች አይለው ቀጥለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በበኩሏ፣ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እንዳልጣሰችና አለመግባባቶችን በንግግር ለመፍታት ዝግጁ መኾኗን በተደጋጋሚ መግለጿ ይታወቃል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢዩ ተድላ፣ በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች በአስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በዘመቻ የማስመለስ ሥራ በቅርቡ እንደሚጀመር፣ በዛሬው መግለጫቸው ላይ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ሦስተኛ ምዕራፍ፣ ዜጎችን በዘመቻ የማስመለስ ሥራ 70ሺሕ የሚደርሱ ዜጎች እንደሚመለሱ ገልጸዋል፡፡ ለዚኽም፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደ’ኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ መዋቀሩንና ዜጎችን የመመለስ ሒደቱን ለማስጀመር ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ያካተተ ልዑክ ከነገ በስቲያ ቅዳሜ ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንደሚያቀና አስታውቀዋል፡፡
በቀን አራት፣ በሳምንት ደግሞ 12 በረራዎችን ለማድረግ መታቀዱንም የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ የማስመለስ ሥራው ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመር አመልክተዋል፡፡ /ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል/