ባለፈው ሳምንት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በቦልቲሞር ከተማ በሚገኝ መስጊድ ተገኝተው፣ የቦልትሞር የሙስሊም ማኅበረሰብ በተባለ ተቋም የእስልምና እምነት ተከታይ ከሆኑ አሜሪካውያን ጋር ተገናኝተው ነበር።
ፕረዚደንቱ ንግግራቸውን ከመጀመራቸው በፊት የ19 ዓመቷ ሰባህ ሙክታር ንግግር አቅርባለች። በጉብኝት ሥነ-ሥርአቱም ላይ ለታዳሚዎቹ ፕረዚደንቱን አስተዋውቃ ነው መልእክቷን የጀመረችው። ሰባህ በቦልቲሞር አውራጃ በሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ፣ የህክምና ተማሪ ናት።
የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በአስተዳደር ዘመናቸው ለመጀመርያ ጊዜ ነው በቦልትሞር ከተማ የሚገኝ መስጊድን የጎበኙበት።
የፕረዝደንቱ የመስጊድ ጉብኝት ለመሆኑ ምን መልእክት ያሳልፋል? ወጣቶችም አሸባሪዎችን እንዳይቀላቀሉ እና ተመልምለው እንዳይገቡ ከሚደረጉት ጥረቶች አንጻር የፕረዚዳንቱ ጉብኝት ምን አንደምታ ይኖረዋል? በማለት ሰባህ ሃሳቧን እንድታካፍለን አርብ በስልክ አነጋግረናት ነበር። በተጨማሪም ባሁኑ ወቅት የተለያዩ የሽብር ጥቃቶችን ተከትሎ፣ በእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ ጥላቻ ይታያል።
ይህ ደግሞ በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አገሮችም ነው ብለንም ጠይቀናት ነበር። ስለዚህ፣ ለየእስልምና ተከታይ ወጣቶች መልእክቷን ስታስተላልፍ፣ ወጣቶች ጥቂቶች በሚፈጽሙት መጥፎ አድራጎት ሁሉም መወቀስ እና መጠላት እንደሌለባቸው ከገለጸች በኋላ፣ ሙስሊም ወጣቶችም ሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር ተቀራርቦ በመስራት ማንነታቸውን እና ሃይማኖታቸውን እንዲያስተዋውቁ ጥሪ አቅርባለች።
ሳሌም ሰለሞን ሰባህ ሙክታርን በስልክ አነጋግራ ያጠናቀረችው ዘገባ አለ። ከዚህ በታች ያለውን የደምጽ ፋይል በመጫን ያድምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5
Your browser doesn’t support HTML5