ሾልኮ የወጣው ሰነድ ከብሔራዊ የጸጥታ ካውንስል ሴክረታሪያት የተገኘ የስለላ ዘገባን የሚጠቅስ ሲሆን ጋና ላይ ሊፈጸም የሚችለው የሽብር ጥቃት ችላ ሊባል የሚችል ነገር አይደለም ይላል። ደብዳቤው ለጋና ኢሚግረሽን አገልግሎት የተላከ ነው።
ሰነዱ ድንበር ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር እንዲደረግ ጥሪ ያቀርባል። ከማሊ፣ ከኒጀርና ከሊብያ የሚገቡ ሰዎችን አጥብቆ መከታተል እንደሚያስፈልግ ይመክራል። ሾልኮ ወጣ የተባለው ሰነድ መጀመርያ ላይ የታየው በማኅበረሰባዊ ሚድያ ላይ ነበር። ከዚያ በኋላ ሰነዱ በሀገር ውስጥ የዜና መገናኛ አውታሮች ወጣ።
የጋናው ፕረዚዳንት ጆን ማሓማ በሬድዮ ባደረጉት ንግግር ሀገሪቱን ለማረጋጋት ጥሪ አቅርብርዋል።“የራሳችን ልዩ ሀይሎች አሰልጥነናል። በአሁኑ ወቅት ከሰለጠኑት ልዩ ሃይሎች መካከል በርከት ያሉት በተጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ። ሊገጥመን ለሚችል ማንኛውም አይነት አደጋ እየተዘጋጀን ነው። ይሁንና ህዝቡም በንቃት እንዲከታተል ያስፈልጋል።” ብለዋል።
ከዐል-ቓዒዳ ጋር የተሳሰረው እስላማዊ መግረብ የተባለው ቡድን ከአቢጃን ወጣ ብሎ በባህር ዳር በሚገኝ መዝናኛ ቦታ ላይ ጥቃት ከፍቶ 19 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ የጋና መንግስት ሀገሪቱ በተጠንቀቅ ላይ እንድትሆን አድርጓል።
ሾልኮ የወጣው ሰነድ እንደሚለው ከአይቮሪኮስት የተገኘው መረጃ ጥቃቱን ያስተባበረው ሰው ያለውን ያካትታል። በጋና ጥቃት የማካሄድ አላማ ያላቸው ሰዎች በኒጀር በተመዘገበች 4 ባራት መኪና ጋና እንደገቡ መረጃው ያመለክታል። አጥቂዎቹ ፈንጂዎችና ሌሎች መሳርያዎች ተለዋጭ የመኪና ጎማ በሚቀመጥበት ቦታ ላይ እንደተደበቁ ሰነዱ ጠቁሟል።
ፕረዚዳንት መሓማ የመረጃው ሾልኮ መውጣት እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል። እንዲህ በግላጭ መውጣት አልነበርበትም ብለዋል።
አያይዘውም እያንዳንዷ የምዕራብ አፍሪቅ ሃገር አደጋ ይጠብቃታል። እኛ ደግሞ ከውጭ ብቻ ሳይሆን ከአገር ውስጥም አደጋ ተደቅኖባታል። ከአሸባሪ ቡድኖቹ ጋር የተቀላቀሉ ዜጎቻችን እንዳሉ ማስረጃ አለን ብለዋል ፕረዚዳንቱ።
የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ዘጋቢ ፍራንሲስካ ካክራ ፎርሶን ከአንካራ የላከችውን ዘገባ አዳነች ፍሰሀየ አቅርባዋለች።
Your browser doesn’t support HTML5