ናይሮቢ ውስጥ በቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳ ውስጥ የተቆራረጡ የዘጠኝ ሴቶች አካላት ጋር በተያያዘ የኬንያ ፖሊሶች ዋናውን ተጠርጣሪ እንደያዙ ተናገሩ፡፡
የብሔራዊ የወንጀል ምርመራ ተቋም ዲሬክተሩ መሐመድ አእሚን እንዳስታወቁት ኮሊንስ ጁማይሲ ኻሉሻ የተባለው የሠላሳ ሶስት ዓመቱ ተጠርጣሪ እአአ ከ2022 ጀምሮ ሚስቱን ጨምሮ 42 ሴቶች ገድያለሁ ሲል ቃሉን ሰጥቷል፡፡ አርባ ሁለት ሴቶች ስለመግደሉ ያቀረበው ማስረጃ የለም፡፡ ነገ ማክሰኞ ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሏል፡፡
SEE ALSO: በናይሮቢ ቆሻሻ መጣያ ሥፍራ ዘጠኝ አስከሬኖች ተገኙከቆሻሻ መጣያው በቅርብ ርቀት ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ብዛት ያላቸው ስማርትፎን ስልኮች እና መታወቂያ ካርዶች ማግኘታቸውን ፖሊሶች አመልክተዋል፡፡
ፖሊሶች እንደተናገሩት ተቆራርጠው የተጣሉት የሴቶች የሰውነት ክፍሎች የተገኙት የአንዲት የደረሰችበት የጠፋ ሴት ዘመድ የሆኑ ሴት ፖሊሶቹን “ በህልሜ አይቻለሁ እና እዚያ ቆሻሻው ጉድጓዱ ውስጥ ፈልጉ” ካሏቸው በኋላ ነው፡፡
ያን ተከትሎም የተቆራረጡ አካላት በጆኒያ ታስረው ቆሻሻ ጉድጓዱ ውስጥ ተገኝተዋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ፖሊሶችን በቸልተኝነት ይወነጅላሉ፡፡
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የሰብዓዊ መብት ቡድኖች ፈርመው ባወጡት መግለጫ የኬኒያ የጸጥታ ተቋማት ደብዛቸው እንዲጠፋ የተደረጉ ሰዎችን በሚመለከት በቀረቡት ሪፖርቶች ዙሪያ የተፋጠነ ክትትል እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
ቀደም ሲል ቆሻሻ ውስጥ የተገኙት አካላት በሰሞኑ የመንግሥት ተቃዋሚ ሰልፎች ላይ የታሰሩ እና የታገቱ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ ተፈጥሮ ነበር፡፡