Your browser doesn’t support HTML5
ኢብራሂም ሻፊ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በተማረባቸው የፍትህ እና ፈለገ ዮርዳኖስ ትምህርት ቤቶች በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ከሚያመጡ ተማሪዎች መካከል አንዱ ነበር። ይሄን ትጋቱን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በጨረሰበት አብዮት ቅርስ(GCA) ትምህርት ቤት በድጋሚ ካሳየ በኃላ በከፍተኛ ነጥብ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲን በመቀላቀል በፖለቲካል ሳይንስ የትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡
ትምሕርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ተወዳጅ የሲቪክ መመሕር ነበር። በትምሕርት ቢሮ ውስጥ በአስተዳደር ሥራም አገልግሏል፡፡ ወደ ጋዜጠኝነት ሞያ የገባው በስፖርት ጋዜጠኝነት ሲሆን፤ ኢትዮ ስፖርት፣ ስፖርት ዓለም አቀፍና መዝናኛ የሥራ መጀመሪያዎቹ ጋዜጦች ነበሩ። በተጨማሪም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የስፖርት ጉዳይ ላይ ትንታኔን በመስጠት ከሚታወቁ ቀዳሚ ጋዜጠኞች አንዱ ነበር። በተለያዩ የሬዲዮ ፕሮግራሞች ላይም የስፖርት ተንታኝ ነበር።
በመጨረሻም “አዲስ ጉዳይ” የተሰኘው ሳምንታዊ መጽሔት ምክትል አዘጋጅ በመሆን ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ የትንተና ጹሑፍ ያስነብብ ነበር። ኢብራሂም በ1997 ዓ.ም ብሔራዊ ምርጫ ወቅት ድብደባና እስር ደርሶበት እግሩ በከፍተኛ ሁኔታ ይታመም እንደነበርና "ሲራመድም ትንሽ ጎተት ያደርገው ነበር" ሲሉ ጓደኞቹ ነግረውናል።
በየካቲት ወር 2008 ዓም የወጣቶችን ስደት በተመለከተ “ኢትዮጵያውያን በተለይ ደግሞ ወጣቶች ለምን ይሰደዳሉ?” በሚል ላዘጋጀነው ፕሮግራም ኢብራሂም የቪኦኤ እንግዳ ነበር።
ኢብራሂም ከጋዜጠኝነቱ በተጨማሪ ተወልዶ ያደገው ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች አብዛኛው ወጣት ለስደት ከሚወጣባት ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወይም "ጨርቆስ" እየተባለ በሚጠራው ሰፈር ነበር “ቂርቆስ አካባቢ በንጽጽር ከሌሎች የአዲስ አበባ ከተሞች ጋር ሲተያይ በኑሮ ዝቅ ያሉ ሰዎች የሚኖሩበት፤ ምግብን ጨምሮ በርካታ ችግሮች ያሉበት አካባቢ ነው” ብሎን ነበር። "ወጣቶቹን የሚያሰድዳቸው ድህነት ነው" ብሎን ነበር።
ኢብራሂም የሚሠራበት “አዲስ ጉዳይ” መጽሔት በመከሰሱና በመዘጋቱ ነሐሴ 3 ቀን 2006 ዓ.ም ከሌሎች የሥራ ባልደረቦቹ አንዱ ሆኖ የስደት ሕይወትን ተቀላቀለ። በመጨረሻው ሰዓት አብሮት የነበረው ጋዜጠኛ ሃብታሙ ስዩም እንደነገረን ኢብራሂም ሻፊ በጠና ታሞ ረቡዕ ታኅሣሥ 25 ቀን 2010 ዓ.ም በናይሮቢ ከተማ ላንጋታ በተሰኘው ክፍለ ከተማ ውስጥ ሕይወቱ አልፏል። አስክሬኑም ወደ ኢትዮጵያ ተልኮ የቀብር ሥነ ስርዓቱ ተፈጽሟል።