የኢራኑ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይሲ ትላንት እሁድ ኢራን ውስጥ በደረሰ የኤሊኮፕተር አደጋ ሕይወታቸው አልፏል።
በአደጋው የሃገሪቱን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሁሴን አሚራብዶላሂያንን ጨምሮ ሌሎችም ባለሥልጣናት መሞታቸው ታውቋል። ሄሊኮፕተሩ ምስራቅ ኢራን ውስጥ አዘርባይጃን በተባለ አውራጃ እንደተከሰከሰ ሲታወቅ፣ የአደጋውን ምክንያት የሃገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን አልገለፀም።
የኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሚኒ ደቀመዝሙር እንደሆኑ የሚነገርላቸው ራይሲ፣ በእ.አ.አ 1988 ዓ.ም. በኢራን በሺሕዎች በሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች፣ ተቃዋሚዎች እና አማፂያን ላይ የሞት ፍርድ ያስተላለፈው ኮሚሽን ቁልፍ ሰው እንደነበሩ ተነግሯል። በኋላም የሃገሪቱን ዩራኒየም የማበልጸግ ፕሮግራም መርተዋል።
SEE ALSO: የኢራንን ፕሬዘዳንት የያዘችው ሄሊኮፍተር ተከሰከሰችየ63 ዓመቱ ራይሲ በእስራኤል ላይ የተፈጸሙትን ከፍተኛ ጥቃቶችን እንደመሩም ይነገርላቸዋል።
መንፈሳዊው መሪ አያቶላህ አሊ ኻሚኒ ዛሬ ሰኞ ምክትል ፕሬዝደንት የነበሩትን ሞሃመድ ሞክበር ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አድርገው ሾመዋል። አምስት የሃዘን ቀናትንም አውጀዋል።
የራይሲ ሞት የመጣው በመካከለኛው ምሥራቅ የእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት መላ ባላገኘበት ወቅት ነው። ባለፈው ወር በእስራኤል ላይ የደረሰው የድሮን እና የሚሳዬል ጥቃት፣ በኻሚኒ መሪነት እና በራይሲ አስፈጻሚነት እንደተከናወነ ተነግሯል።
በሄሊክፕተሩ አደጋ የተረፈ ሰው እንደሌለ ኢራን በይፋ ማስታወቋን ተከትሎ፣ ጎረቤት ሃገራትና ሌሎችም የኢራን ወዳጆች የሃዘን መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የቻይናው ፕሬዝደንት ሺ ጂንፒንግ ሃገራቸው “ጥሩ ወዳጅ” እንዳጣች ባስተላለፉት የሃዘን መግለጫ አስታውቀዋል።
ራይሲ በሥልጣን ዘመናቸው “የኢራንን ፀጥታና መረጋጋት በመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል” ብለዋል ሺ ጂንፒንግ።